ከአድዋ እስከ ብሪክስ የዘለቀው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከፍታና የቀጣናው ተጽዕኖ ፈጣሪነት

AMN- ጥቅምት 5/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ስትራቴጂካዊና ታሪካዊ ቦታ በመጠቀም በዲፕሎማሲው ዘርፍ በርካታ አበይት የስኬት ከፍታዎችን ማስመዝገብ ችላለች።

ኢትዮጵያ የነፃነት ምልክት በመሆኗ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የነበራትና ያላት የዲፕሎማሲ ሚና ልዩና የጎላ ነው።

ይህ የታሪክ አደራ፣ የአፍሪካውያን ወንድማማችነትና የሉዓላዊነት ጽናት ሃገሪቱን ከአህጉራዊ መሪነት እስከ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪነት አሸጋግሯታል።

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ትልቁ መሠረትና የመጀመሪያው የታሪክ ከፍታ በ1888 ዓ.ም የተቀናጀችው የአድዋ ድል ነው። የዓለም ኃያላን ሃገራት አፍሪካን በተቀራመቱበት በዚያ ወቅት ኢትዮጵያ ነፃነቷን አስከብራ በድል መውጣቷ፣ የታሪክን አቅጣጫ የቀየረ ክስተት ነበር።

ይህ ታላቅ ድል የአውሮፓ ሃገራት ከኢትዮጵያ ጋር ቀጥታ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዲመሠርቱ፣ ኤምባሲዎቻቸውን እንዲከፍቱ እና የሃገሪቱን ሉዓላዊነት እንዲቀበሉ አድርጓል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ህግ፣ በሕግ የበላይነት እና በጋራ ደህንነት ላይ የነበራትን ጽኑ እምነት በተግባር አስመስክራለች፡፡

ኢትዮጵያ ለአህጉሯ ያበረከተችው አስተዋጽዖ በአፍሪካ የታሪክ ድርሳናት ውስጥ በደማቁ የተጻፈ ነው፡፡

እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ዚምባብዌ እና ናሚቢያ ላሉ ሃገራት የገንዘብ፣ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ መስጠቷ በአህጉሪቱ ዘንድ ከፍተኛ ክብር እንድታገኝ አድርጓታል።

ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበርን በተመለከተም በኮሪያ፣ ኮንጎ፣ ላይቤሪያ፣ ሱዳንና ሶማሊያ ግዳጆችን በመወጣት በዩ ኤን የሰላም ማስከበር ግንባር ቀደም ሃገር ሆናለች።

በቅርብ ዓመታት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ትኩረቱን ወደ ኢኮኖሚ ዕድገት፣ የኃይል አቅርቦትና ቀጣናዊ ትስስር አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሆና መመረጧ በዓለም አቀፍ የጂኦ-ፖለቲካና የኢኮኖሚ መድረክ ላይ ያላትን ተፅዕኖ ፈጣሪነት የሚያሳይ ትልቅ የስኬት ማረጋገጫ ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የመሳሰሉ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም የመገንባትና ጎረቤት ሃገራትን በኤሌክትሪክ ኃይል የማስተሳሰር ሥራ አገሪቱን የቀጣናው የኃይል መሠረት አድርጓታል።

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከፍታ መሠረቱ የታሪክ አደራ፣ የአፍሪካውያን ወንድማማችነት እና የነፃነት ምልክትነት ነው።

ሃገሪቱ ከታሪካዊው የአድዋ ድል ጀምሮ እስከ አሁኑ የብሪክስ አባልነትና የቀጣናው መሪነት ድረስ ያሳየችው የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ጥንካሬዋንና ተፅዕኖዋን በግልጽ ያሳያል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review