የካቲት 14/2018
የአዲስ አበባ ከተማ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ “ኢትዮጵያ ታምርት፣አዲስ አበባ ትበልጽግ” በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጀዉ 5ኛው የኢትዮጵያ ታምርት ባዛር እና ኤግዚቢሽን ተከፍቷል፡፡
ባዛር እና ኤግዚቢሽኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከሌሎች የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ከአዲ አበባ ከተማ አመራቾች ጋር በመሆን በይፋ አስጀምረዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት አዲስ አበባ ከተማ የአለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከል፣የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እና የኢትዮጵያ መዲና እንደሆነችው ሁሉ የኢንዱስትሪ ማዕከል ሆና እያገለገች ትገኛለች ብለዋል፡፡
ዜጎች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እዲሆኑ ከለውጡ ወዲህ በዘርፉ አያሌ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል ያሉት ከንቲባ አዳነች በዚህም በጽናት እና በትጋት በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዜጎች ብርቱ ጥረት እየተገነባች በሁሉም፣ለሁሉም እና ከሁሉም በሆነ ትጋት ጸንታ እየቀጠለች መሆኗን የጠቆሙት ከንቲባዋ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለሀገር ሉዓላዊነት እና አንድነት መከታ እና ጋሻ ሆነው ያገለግላሉ ብለዋል፡፡
ለዚህም በምግብ እራስን መቻል ሀገር በቀል ምርቶችን መጠቀም በጠቅላላው የኢኮኖሚ ብልጽግናን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡
ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ጎዳና የሰብዓዊ ክብር ከፍታ ማሳያ እንደሆነ ሁሉም እኩል ሊገነዘበው ይገባልም ብለዋል ከንቲባ አዳነች፡፡
አልቆ ማለም መሰረታችን፤ ከችግር በላይ ከፍ ብሎ መብረር የብልጽግና አምዳችን ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች የዜጎችን ተጠቃሚነት በተሻለ ደረጃ ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገትን ማረጋገጥ የሚቻለው ፈጣን፣አካታች እና ዘላቂ የአምራች ኢንዱስትሪዎች እድገት ማፋጠን ሲቻል ነው፡፡
ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት እና በማሳደግ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃነት ማረጋገጥ እደሚገባም አጸንዖት ሰጥተዋል፡፡
በአዲስ አበባ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ቀዳሚ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ መሆኑን የገለጹት ከንቲባ አዳነች የዘርፉን ተግዳሮት በመፍታት ከተማዋን የኢንዱስትሪ ማዕከል ማድረግ የከተማ አስተዳደሩ የርብርብ ማዕከል መሆኑን ተናረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አምራቹን ለማበረታታት የፋይናንስ አቅርቦት በማመቻት፣የመስሪያ እና ማምረቻ ቦታዎችን በማቅረብ፣የመሰረተ ልማት ማስፋፊያዎችን በማከናወን፣አስፈላጊ የሙያ ስልጠናዎችን በመስጠት የኢንቨስትመንት መሬት በማቅረብ እና ፈጣሪ እጆችን በማበረታታት በብዙ ሂደት እየተጓዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሃብታሙ ሙለታ