ሐዋሳን የአፍሪካ ኩራት እና የኢትዮጵያ ተስፋ እናደርጋታለን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing ሐዋሳን የአፍሪካ ኩራት እና የኢትዮጵያ ተስፋ እናደርጋታለን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – የካቲት 15/2018 ዓ.ም.

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በሐዋሳ ከተማ በደማቅ ወታደራዊ ሥነ-ሥርዓት ተከብሯል።

በክብረ በዓሉ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ሐዋሳ የሲዳማ ክልል ብቻ ሳትሆን የኢትዮጵያ ራዕይ የሚሰነቅባትና የአፍሪካ ኩራት፣ የብልጽግና ተምሳሌት ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ወቅት ኢትዮጵያ ድህነትን ታሪክ አድርጋ በመቅበር ለመላው አፍሪካ ምሳሌና ኩራት እንደምትሆን አጽንኦት ሰጥተዋል።

መጪው ትውልድ ድህነትን በታሪክ መዝገብ ላይ ብቻ የሚያውቅባትን የበለጸገች ሀገር ለመገንባት መንግሥታቸው የጸና ቁርጠኝነት እንዳለውም አረጋግጠዋል።

ይህንን ሀገራዊ ራዕይ ለማሳካት የሚደረገው ጉዞ በዋዛ ፈዛዛ የሚሳካ ሳይሆን ከፍተኛ መስዋዕትነትን የሚጠይቅ መሆኑን ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ላባችንን አንጠፍጥፈን፣ ደማችንን አፍስሰንና አጥንታችንን ከስክሰን ኢትዮጵያን፣ ሲዳማን፣ ሐዋሳንና አፍሪካን እንገነባለን ብለዋል።

የሐዋሳ ከተማን የልማት ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ሕዝቡ ከከንቲባውና ከክልሉ መስተዳድር ጎን በጽናት እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

እስካሁን በከተማዋ የታየው ለውጥና ዕድገት ከከተማዋ ሰፊ አቅም አንጻር ሲታይ አንድ በመቶ ብቻ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በቀጣይ ሐዋሳን ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችና ኩነቶች በስፋት የሚስተናገዱባት እንዲሁም በርካታ አፍሪካውያን መጥተው የሚጎበኟት ታላቅ የፍቅር መዲና ለማድረግ መንግሥትና ሕዝብ በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በቀጣይ ወደ ከተማዋ ሲመለሱ ነዋሪዎቹ አዳዲስ ታሪኮችን፣ ድሎችንና ስኬቶችን ይዘው እንደሚገናኙ ያላቸውን ሙሉ ዕምነት ገልጸዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review