የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አከራካሪ የሆኑ ምርጫ ክልሎችን በተመለከተ የተላለፈውን ውሣኔ ይፋ አደረገ

You are currently viewing የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አከራካሪ የሆኑ ምርጫ ክልሎችን በተመለከተ የተላለፈውን ውሣኔ ይፋ አደረገ
  • Post category:ፖለቲካ

AMN የካቲት 16/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአማራ እና በትግራይ ክልላዊ መንግሥታት አከራካሪ የሆኑት ምርጫ ክልሎችን በተመለከተ ውሣኔ አስተላልፏል።

የምርጫ ቦርድ የውሳኔ ሐሳብ እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ቦርዱ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የጊዜ ሠሌዳ ላይ በተመለከተው መሠረት ጥር 22 ቀን 2018 ዓ.ም. የመራጮች ምዝገባ ለማካሄድ እየተዘጋጀባቸው ያሉትን ምርጫ ክልሎችና ምርጫ ጣቢያዎች ዝርዝር ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

ይህንኑ ቦርዱ ያወጣውን የምርጫ ክልሎችና ጣቢያዎች ዝርዝር ተከትሎ ጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም. የፌዴሬሽን ምክር ቤት በቁጥር ፌደም/አፌ/5/13138 ለቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ በትግራይ እና በአማራ ክልላዊ መንግሥታት መካከል አከራካሪ ሆነው የቆዩት የአምስት ምርጫ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄው እስከሚፈታ የሁመራ፣ የአዲረመፅ፣ የኮረም አፍላ፣ የጠለምትና የራያ አላማጣ ምርጫ ክልሎች ከትግራይ ክልላዊ መንግሥት ውጪ ሆነው ለብቻቸው በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እንዲደረግ ምክር ቤቱ መወሰኑን ለቦርዱ አሳውቋል።

የክልል ምክር ቤት ምርጫው በአካባቢዎቹ ላይ የተነሳው የይገባኛል ውዝግብ በሕገ-መንግሥት ውሳኔ ሲፈታ አመቺ ጊዜ ተመርጦ ወደፊት እንዲካሄድ መወሰኑንም እንዲሁ ምክር ቤቱ አሳውቋል።

በመሆኑም ቦርዱ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከላይ በተጠቀሰው አግባብ ለመፈጸም የሚያስችለውን ሕግና ሥርዓት በመጠበቅ ተግባራዊ የሚያደርግ መሆኑን እሳውቋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review