የካቲት የጥቁር ህዝቦች ደማቅ የታሪክ ወር እና አድዋ

You are currently viewing የካቲት የጥቁር ህዝቦች ደማቅ የታሪክ ወር እና አድዋ

የካቲት ወር እና የአድዋ ድል ለጥቁር ሕዝቦች ሥነ-ልቦናዊ ነፃነት ያላቸው ቁርኝት እጅግ ጥልቅ ነው። የካቲት በኢትዮጵያ የታሪክ የዘመን አቆጣጠር የድል ዋዜማና የድል ወር ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይ በሰሜን አሜሪካ የጥቁር ሕዝቦች የታሪክ ወር (Black History Month) ተብሎ የሚከበርበት ወቅት ነው።

የጥቁሮች ታሪክ ወር (Black History Month) እንዴት ተጀመረ?

የጥቁሮች ታሪክ ወር ለመጀመሪያው ጊዜ እ.ኤ.አ. በ1926 “የጥቁሮች ታሪክ ሳምንት” ተብሎ በየካቲት ሁለተኛ ሳምንት ማክበር ተጀመረ። የካቲትን የመረጡት ለጥቁሮች መብት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ አብርሃም ሊንከን ባርነትን በሕግ ያገዱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እና ፍሬድሪክ ዳግላስ ከባርነት አምልጦ ለጥቁሮች ነፃነት የታገለ ታዋቂ ግለሰቦች የልደት ቀን በዚህ ወር ስለሚውል ነው፡፡

ከዚህ በመነሳት በ1960ዎቹ የጥቁር መብት ተሟጋች ተማሪዎች ባደረጉት ግፊት በ1976 ፕሬዝዳንት ጄራልድ ፎርድ ወሩን በይፋ “የጥቁሮች ታሪክ ወር” ብለው አወጁ።

የካቲት ወር ለጥቁር ሕዝቦች ልዩ ትርጉም ያለው ወር ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የጥቁሮች ታሪክ ወር ተብሎ ሲከበር፣ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ የአድዋ ድል የተገኘበት ታላቅ ወር ነው።

አድዋ የነፃነት እና የኩራት ተምሳሌት

የአድዋ ድል የአጋጣሚ ሳይሆን የተቀናጀ ወታደራዊ ስልት፣ የዲፕሎማሲ ጥበብ እና የአንድነት ውጤት ነው። ጥቁር ሕዝቦች ነጭ ወራሪን ማሸነፍ እንደሚችሉ በተግባር ያሳዩበት የመጀመሪያው ታላቅ ድል ነው። ይህም በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች “እኛም ማሸነፍ እና ራሳችንን ማስተዳደር እንችላለን” የሚል የተስፋ ብርሃን ሆኗቸዋል።

የፓን-አፍሪካኒዝም መንፈስ

የአድዋ ድል ለፓን-አፍሪካኒዝም (Pan-Africanism) እንቅስቃሴ መወለድ ትልቁ መሠረት ነው። የጥቁሮች ታሪክ ወር ሲከበር፣ ስለ አፍሪካውያን መብትና ነፃነት የሚነሱ ታሪኮች ሁሉ መነሻቸው ኢትዮጵያ በአድዋ ያስመዘገበችው ድል ነው። ብዙ የአፍሪካ አገራት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ (አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ) ቀለማት ለባንዲራቸው መምረጣቸው የዚህ ትስስር ውጤት ነው።

በጥቁሮች ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት የሚባለው ስም ለፖለቲካዊ ንቅናቄ ትልቅ ቦታ አለው። ጥቁር አሜሪካውያንና በካሪቢያን የሚኖሩ ጥቁሮች በጭቆና ውስጥ በነበሩበት ወቅት፣ አድዋንና ያልተገዛችውን ኢትዮጵያን እንደ መንፈሳዊ ጥንካሬ ይቆጥሩ ነበር። የካቲት ወር እነዚህን የጥቁር ሕዝብ የትግል ታሪኮች የምንዘክርበት ወቅት በመሆኑ አድዋ የዝግጅቱ ዋነኛ ማጠንጠኛ ይሆናል።

የካቲት እና አድዋ የታሪክ አጋጣሚ

ሁለቱ ኩነቶች በየካቲት ወር ላይ መውደቃቸው አንድም የአድዋ ድል በዓል በካቲት ወር ላይ መከበር፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሙሉ የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ወር (Black History Month) መሆኑ ነው። አድዋ ለጥቁሮች ታሪክ ወር ተጨባጭ የድል ማረጋገጫ ሲሆን፣ የጥቁሮች ታሪክ ወር ደግሞ ለአድዋ ድል ዓለም አቀፋዊ እውቅናን የሚሰጥ ክስተት ነው።

አድዋ ድል ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሕዝብ የስነ-ልቦና ነፃነት አዋጅ ነው። በዚያ ዘመን ጥቁር ሕዝቦች እንደ “ደካማ” እና “ባሪያ” በሚታይበት ወቅት፣ ኢትዮጵያዊያን ዓለምን ያስደነገጠ ድል ማስመዝገባቸው የታሪክን አቅጣጫ ቀይሮታል።

የአድዋ ድል በምዕራቡ ዓለም ለነበሩ የጥቁር ሕዝቦች መብት ተሟጋቾችና መሪዎች ተራ የጦርነት ድል ሳይሆን፣ የጥቁር ሕዝብ ትንሳኤ ተደርጎ ነበር የሚወሰደው። እነ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ማልኮም ኤክስ እና ማርከስ ጋርቪ ኢትዮጵያንና አድዋን እንደ ሥነ-ልቦናዊ መከታ ተጠቀሙባቸዋል፡፡

ማርከስ ጋርቪ የፓን-አፍሪካኒዝም አባት ተደርጎ ይወሰዳል። ለአድዋ ድል ትልቅ አክብሮት ነበረው። ጋርቪ ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን ኩራት ናት በማለት ጥቁሮች በባርነት ተገዝተው ሳለ፣ ኢትዮጵያ ግን በአድዋ ድል ምክንያት ራሷን የቻለች መንግሥት መሆኗን ለትግሉ እንደ ማቀጣጠያ ተጠቅሞበታል።

ሁለንተናዊ የጥቁር ሕዝቦች መሻሻል ማህበር (UNIA) ሲመሠርት፣ በዝማሬዎቻቸው ውስጥ “ኢትዮጵያ ሆይ ተነሺ” የሚሉ ግጥሞችን በማካተት የጥቁር ሕዝቦችን ሞራል ይገነባ ነበር።

ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ በ1957 (እ.ኤ.አ) የጋናን የነፃነት በዓል ለማክበር አፍሪካ በመጣበት ወቅት፣ ስለ ኢትዮጵያና ስለ አድዋ ድል ያለውን አድናቆት ገልጿል።

ኪንግ ጥቁር አሜሪካውያን ለመብታቸው በሚታገሉበት ወቅት፣ ኢትዮጵያን እንደ የነፃነት ተስፋ ይመለከታት ነበር። አድዋ ለኪንግ የሚያሳየው ነገር ቢኖር፣ ጥቁር ሕዝብ በሰላማዊ መንገድም ሆነ በቆራጥነት መብቱን ማስከበር እንደሚችልና በታሪክ ውስጥ “ባሪያ” ብቻ ሆኖ እንዳልኖረ ማረጋገጫ ሆኖታል።

ማልኮም ኤክስ ከጥቁር አሜሪካውያን መሪዎች መካከል ለአፍሪካ አንድነት ትልቅ ትኩረት የሰጠ መሪ ነበር። ማልኮም አድዋን የሚያየው እንደ አንድነት ውጤት ነው። “ኢትዮጵያውያን በአድዋ ያሸነፉት በዘር ወይም በጎሳ ሳይከፋፈሉ እንደ አንድ ጥቁር ሕዝብ ስለቆሙ ነው” የሚለውን ትምህርት ለአሜሪካ ጥቁሮች ያስተምር ነበር።

ማልኮም ጥቁር ሕዝብ ራሱን ከነጮች የበታች አድርጎ የሚያይበትን ለመስበር፣ የአድዋን ድል እንደ ታሪካዊ ማስረጃ ይጠቅስ ነበር።

በአጠቃላይ የካቲት ወር ለጥቁር ሕዝብ የክብር ወር ነው። አድዋ የአካል ነፃነትን ሲያበስር፣ የካቲት ደግሞ የአእምሮ ነፃነትን በማጠናከር ጥቁር ሕዝቦች አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲጓዝ የሚያደርግ የብርሃን ወር ነው።

በቶለሳ መብራቴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review