አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ‘ቡቤ’ የተሰኘ ሲትኮም ድራማ ለማስጀመር ከጃንኮ ፕሮዳክሽን ጋር የሥራ ስምምነት ተፈራረመ

You are currently viewing አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ‘ቡቤ’ የተሰኘ ሲትኮም ድራማ ለማስጀመር ከጃንኮ ፕሮዳክሽን ጋር የሥራ ስምምነት ተፈራረመ

AMN – የካቲት 19/2018 ዓ.ም

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ‘ቡቤ’ የተሰኘ ሲትኮም ድራማ ለማስጀመር ከጃንኮ ፕሮዳክሽን ጋር የሥራ ስምምነት ተፈራርሟል።

ተቋሙ የትውልዱን ፍላጎት የሚያሟሉ ይዘቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ በፊርማ ስነስርዓቱ ወቅት ገልፀዋል።

አቶ ካሳሁን ጎንፋ እንደገለጹት፤ ኤኤምኤን አሁን ላይ እያደገ የመጣውን የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ፍላጎት ለማሟላት በኪነ-ጥበብ ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል። “ተጨማሪውን ኤኤምኤን ፕላስ ቻናል ካቋቋምን በኋላ የህዝባችንን የሚዲያ ጥማት ደረጃ በደረጃ እያረካን ነው” ብለዋል።

አቶ ካሳሁን አክለውም፤ አዲስ አበባ ለኪነ-ጥበብ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የቲያትር ቤቶችንና የኪነ-ጥበብ ማቅረቢያ አደባባዮችን እያሰፋች መሆኑን ጠቅሰው፣ ጥበባዊ ይዘቶችን ማምረት ደግሞ የአርቲስቶችና የሚዲያ ተቋማት ድርሻ መሆኑን ገልጸዋል።

ከጃንኮ ፕሮዳክሽን ጋር የተደረገው ስምምነት የተመልካቾችን ፍላጎት የሚያሟላና የወጣቶችን ጥያቄ የሚመልስ በመሆኑ፣ የከተማነት ገጽታን የሚያንፀባርቁ ይዘቶችን ለተመልካች ለማድረስ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ተብራርቷል።

የጃንኮ ፕሮዳክሽን መስራች ዋቆ ጌታቸው በበኩሉ፤ ኤኤምኤን ከአዲስ አበባ ለውጥ ጋር አብሮ የሚራመድ ሚዲያ በመሆኑ አብሮ ለመስራት በመወሰናቸው መደሰቱን ገልጿል። ‘ቡቤ’ የተሰኘው አዲስ የኮሜዲ ሲትኮም በኤኤምኤን ፕላስ ሲቀርብ ለይዘትና ለጥራት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አረጋግጧል።

በተገኝ በፍቃዱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review