AMN- የካቲት 19/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ማዕከል መሆኗ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎችን እያስገኘ መሆኑ ተገለጸ፡፡
አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና እና የዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች ማዕከል መሆኗ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአህጉሪቱም የሚሰጠው ፋይዳ እጅግ ከፍተኛ ነው። ከተማዋ “የአፍሪካ ብራስልስ” እየተባለች እስከመጠራት የደረሰችው ያለምክንያት አይደለም።
ከተማዋ የዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ማዕከል መሆኗ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች እያስገኘ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላም እና ደህንነት መምህርና ተመራማሪ ሙሉጌታ አየለ ( ዶ/ር) ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡
አዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መቀመጫ መሆኗ፣ ከተማዋን የአህጉሪቱ የፖለቲካ ውሳኔዎች ማዕከል ያደርጋታል።

ይህ ደግሞ የሀገሪቷን ፖለቲካዊ ተሰሚነት እና ስትራቴጂካዊ ተፅዕኖ ከፍ ያደርጋል ሲሉ ሙሉጌታ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በርካታ ዓለም ዓቀፍ እና የአህጉሪቱ ዋና ዋና ስብሰባዎች በአዲስ አበባ ከተማ መካሄዳቸው ኢትዮጵያ ከአጀንዳ ቀራጭነት ሚና ባለፈ፣ በአህጉራዊ እና ዓለም ዓቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የራሷን አቋም ለማንጸባረቅና ተፅዕኖ ለማሳደር ቅርብ እንድትሆን ያደርጋታልም ብለዋል።
ከ100 በላይ አገራት ኤምባሲዎቻቸውን በአዲስ አበባ ከተማ መክፈታቸው፣ ከተማዋን በዓለም ላይ ካሉ ከፍተኛ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ከሚኖርባቸው ከተሞች አንዷ አድርጓታል ያሉት መምህርና ተመራማሪው፣ ይህ ለሁለትዮሽ እና ለባለብዙ ወገን ድርድሮችና ውይይቶች አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።
የኮንፈረንስ ቱሪዝም የአገርን ገጽታ በመገንባት ረገድ ያለውን ፋይዳ የገለጹት ሙሉጌታ (ዶ/ር) በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ መሪዎች፣ ምሁራን እና ጋዜጠኞች ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ፣ የአገሪቱን ሰላም፣ እንግዳ ተቀባይነት እና ዘመናዊነት በተግባር እንደሚያዩ ተናግረዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ላይ ያላትን ተቀባይነት ያሳድጋል፤ በሂደትም ለስላሳ ኃይል (Soft Power) መገንቢያነት ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ እንግዶች በሚመጡበት ጊዜ የአገሪቱን ታሪክ፣ ምግብ፣ ቡና እና አንዳንድ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ባህላዊ እና ሌሎቸ የስጦታ ቁሳቁሶችን ይገዛሉ፤ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የባህል ተፅዕኖዋን እንድታሰፋ ይረዳታል ሲሉ የሰላም እና ደህንነት መምህርና ተመራማሪው ተናግረዋል።
የኮንፈረንስ ቱሪዝም ቀጥተኛ የኢኮኖሚ ጥቅም እንዳለው ያነሱት ሙሉጌታ (ዶ/ር) ይህም ማለት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እንግዶች ለሆቴል፣ ለትራንስፖርት እና ለገበያ የሚያወጡት ወጪ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል ብለዋል።
የኮንፈረንስ ማዕከል ለመሆን የግድ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ አየር መንገዶች፣ ሆቴሎች እና የመገናኛ አውታሮች ያስፈልጋሉ። ይህ ደግሞ ለከተማዋ ዘመናዊነት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
አዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዚህ ረገድ በርካታ ስራዎችን ሰርታለች፤ እየስራችም ትገኛለች፡፡
በቶለሳ መብራቴ