“ጊዜ ወርቅ ነው” የሚለው አባባል የተለመደ ነው፡፡ አባባሉ የጊዜን ውድነት እና ከፍ ያለ ዋጋውን ያሳያል፡፡ ይህ ውድ፣ ከውድም በጣም ውድ የሆነው ጊዜ፤ ለሁሉም ሰው በፍትሐዊነት የተሰጠው ልዩ ተፈጥሯዊ ስጦታ መሆኑ፤ በጊዜ የመጠቀምም ሆነ ያለመጠቀም ውሳኔ በእያንዳንዱ ሰው ላይ እንዲወድቅ አድርጎታል፡፡ ለዚህም ነው፤ በምድር ላይ ከልደት እስከ ሞት ድረስ ውስን የሆነ ዕድሜን የሚኖረው የሰው ልጅ ከጊዜ ጋር ባለው ቁርኝትና አጠቃቀም፣ የሕይወት ዘመኑን ስኬት እና ውድቀት የሚወስነው።
የጊዜን ወርቅነት ያለመረዳት፣ በጊዜም በአግባቡ ያለመጠቀም ችግር በኢትዮጵያዊያን ዘንድ በስፋት የሚስተዋል ችግር ሆኖ ቆይቷል። “የሐበሻ ቀጠሮ” የሚል ስያሜ እስከመሰጠት ያደረሰን፣ ለጊዜ ያለን ዋጋ ቀላልና ርካሽ መሆኑ ነው፡፡ ጊዜን ማባከን ለውድቀትና ለኋላቀርነት ራስን በጓደኝነት አሳልፎ እንደመስጠት ይቆጠራል፡፡ የጊዜ አባካኝነት በዓለማዊው አስተምህሮ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊው አስተምህሮም የተወገዘ ነው፡፡ ምክንያቱም፤ በሰከንድ፣ በደቂቃ፣ በሰዓት፣ በቀን፣ በሳምንት፣ በወር፣ በዓመት … ተለክቶ በተሰጠ ጊዜ ውስጥ በታቀደና ውጤታማ በሆነ መልኩ አለመንቀሳቀስ በስጋም ሆነ በነፍስ ጉድለት የሚያስከትል እንደሆነ ይታመናል፡፡
ውድ አንባቢያን፤ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ምን ያክል ውጤት እንደሚያመጣ የሁላችን መዲና የሆነችውን አዲስ አበባን በማሳያነት እንመልከት፡፡ ምልከታችንን በጊዜ እንወስነው፡፡ ከ2010 ዓ.ም በመነሳት አሁን እስካለንበት (ግንቦት አጋማሽ 2018 ዓ.ም.) ድረስ ባለው የጊዜ ገደብ ውስጥ እንመላለስ፡፡ የእያንዳንዱን የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢዎች የቀደመ ገፅታ እና አሁናዊ መልክ እናስታውስ፡፡ በኮሪደር ልማት፣ በወንዝ ዳርቻ ልማት፣ በተለያዩ እና ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ሰጪ ግዙፍ ፕሮጀክቶች … የተሠሩ እና ለውጤት የበቁ ትሩፋቶችን እስከምንችለው ድረስ እንቁጠር፡፡ የከተማዋን እየተጋጋለ የመጣውን የእንቅልፍ አልባ እንቅስቃሴዎችም በትውስታችን ላይ እናክልበት፡፡ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በአዲስ አበባ ለታየውና እየታየ ላለው ሁሉን አቀፍ አስደናቂ ስኬት እንዲመዘገብ ካስቻሉ ቁልፍ አቅሞች መካከል፡- ጊዜን በአግባቡ የመጠቀም ባህልና ልምድ መዳበሩ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡
ከቀናት በኋላ፤ የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል በመላው የሀገራችን የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀትና በመንፈሳዊ ሥነ-ስርዓት ይከበራል። እንደ እምነቱ አስተምህሮ በዓሉ የሚከበረው፤ የታላቁን ነቢይ ኢብራሂምና የልጃቸውን የኢስማኤልን ፍጹም ታዛዥነት፣ ታማኝነትና ለመስዋዕትነት የመዘጋጀት ጥግን ለማስታወስ ነው። በዚህ የበዓሉ መሰረታዊ መነሻዎች ውስጥ “መስዋዕትነት” አንዱ ሆኖ እንመለከታለን። ይህም በዓሉ፣ ራስን ለአምላክ ትዕዛዝ ፍጹም አሳልፎ ከመስጠት መንፈሳዊ እውነት በዘለለ፣ “መስዋዕትነት” የተሰኘውን ታላቅ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊና ሀገራዊ እሴት በሰፊው የሚሰላሰልበት ነው፡፡

መስዋዕትነት በብዙ የሕይወት ዘርፎችና በተለያዩ ተግባራዊ መልኮች ሊገለጽ የሚችል ሰፊ ጽንሰ-ሀሳብ ነው። ከእነዚህ ዘርፈ-ብዙ የመስዋዕትነት መገለጫዎች መካከል ደግሞ የሰው ልጅ ሊተካውና ሊመልሰው የማይችለው እጅግ ውድና ታላቁ ሀብት “ጊዜ” እንደሆነ ይታመናል። አዎ፤ ይህንን ለመረዳት ሩቅ ሳንሄድ አዲስ አበባን መመልከት ይበቃል። ዛሬ በአይናችን የምናያት፣ በየቀኑ አዳዲስ ገጽታዎችን የምትላበሰውንና በግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች አሸብርቃ የነገ እጣ ፈንታዋን በደመቀ ሁኔታ እየቀየረች ያለችውን የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባን ስንመለከት፣ ይህንን እውነት በተግባር እንረዳዋለን። መዲናዋ አሁን ያለችበትን አንጸባራቂ የለውጥ ምዕራፍ ልታስመዘግብ የቻለችው፣ ይህንኑ የመስዋዕትነት ፍልስፍና ወደ ተግባር በመተርጎም፣ የጊዜን ዋጋ ተረድታ ሳምንቱን ሙሉ በቀን 24 ሰዓት ያለማቋረጥ መሥራት በመቻሏ እንደሆነ ግልጽ ነው።
ጊዜ በመስዋዕትነት የሚቀርብ ውድ ስጦታ ስለመሆኑ ከእስልምና ኃይማኖት አስተምህሮ ጋር በማያያዝ የሚያስረዱት አየር ጤና የሚገኘው አንሷር መስጂድ ኃይማኖታዊ መምህር የሆኑት ዑስታዝ ሙሐመድ ፈረጅ ናቸው። እሳቸው እንደሚገልጹት፤ በእስልምና አስተምህሮት፣ ጊዜ ከምንም በላይ ውድ ነው፡፡ ጊዜ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ጊዜ እንደ ተጠቃሚው ብቃት ውጤት የሚሰጥ ነው፡፡ ጊዜን ካልቆረጥከው ይቆርጥሃል። በቅዱስ ቁርዓን ውስጥ ስለጊዜ በብዙ ቦታዎች ላይ ተጠቅሷል፡፡ ‘ጊዜውን የተጠቀመ ዳነ፣ ተረፈ፣ የሚፈልገውን አገኘ፡፡ ጊዜውን ያልተጠቀመ ደግሞ ከሰረ፣ ተዋረደ፣ የሚፈልገውን አጣ፣ ወደቀ’ የሚል መልዕክት በተለያዩ የቅዱስ መጽሐፍቱ ላይ ተጠቅሶ እናገኛለን። ስለዚህ ጊዜውን በአግባቡ የተጠቀመ ይድናል፣ የተሻለ ሕይወትን ይኖራል፡፡ በተቃራኒው ጊዜውን ያባከነ ይዋረዳል፣ ለጉዳትም ይዳረጋል፡፡
ዑስታዝ ሙሐመድ አክለው እንዳስረዱት፤ ጊዜን ሳይባክን በአግባቡ መጠቀም ይገባል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ነብዩ መሐመድ፤ “ሁለት ጸጋዎች አሉ። አንደኛው ጤንነት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ጊዜ ነው፡፡ በእነዚህ ጸጋዎች ላይ አብዛኛው ሰው ተሞኝቶባቸዋል።” በማለት ማስተማራቸውን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ ይህም፤ የሰው ልጅ በቀላሉ በእጁ ያሉትን ሀብቶች (ጊዜና ጤናን) ሳያባክን መጠቀም እንዳለበት የእምነቱ አስተምህሮ ደጋግሞ እንደሚገልጽ አንስተዋል፡፡
“በኢድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል ላይ በግን በማረድ ብቻ መስዋዕትን መግለፅ በቂ አይደለም፡፡ ይልቁንም ጊዜያችንን ሰውተን ወዳጅ ዘመዶችን፣ ጎረቤቶችን፣ አቅመ ደካሞችን፣ የተቸገሩትን መጠየቅና ካለን ማካፈል ይጠበቅብናል፡፡” ያሉት ዑስታዝ ሙሐመድ፤ ጊዜን ለልማት ማዋል፣ የሰው ልጅ ለተሻለ ሥራ እንዲነሳሳ፣ ሞራሉ እንዲገነባ፣ አንድነት እንዲፈጠር፣ ሠላም እንዲሰፍን … ማዋል የሚያስገኘው ስጋዊና መንፈሳዊ ውጤት ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተለይ ጊዜን ለልማት ማዋል እጅግ ወሳኝ መሆኑን ነብዩ መሐመድ በተለያዩ ምሳሌዎች ካስተማሯቸው ትምህርቶች መካከል አንዷን በመጥቀስ አብራርተዋል፤ “ከሃያ ወይም ከረጅም ዓመት በኋላ ፍሬ የምታፈራን ተክል፣ ‘ነገ ትሞታላችሁ፣ ነገ የዓለም ፍጻሜዋ ነው’ ብትባሉ እንኳን፤ ተክሏን ባላችሁ ጊዜ ወይም አሁኑኑ ትከሏት’ ይላሉ። ምክንያቱም፣ ዛሬ ላይ ያለው ሰው ተክሏን ካልተከላት፣ ከሃያ ዓመት በኋላ የሚመጣው ትውልድ ከፍሬዋ ሊመገብ አይችልምና፡፡ ከዚህ የምንረዳው፤ ልማት ፈፅሞ መቆም እንደሌለበት ነው፡፡ በችግር ውስጥም ሆኖ ማልማት፣ በሕመም ውስጥም ሆኖ መሥራት፣ በምሽትም ሆነ በሌሊት የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል ይገባል፡፡ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢከሰቱ እንኳን ለእነሱ መፍትሄ እየሰጡ ልማትን ያለማቋረጥ ማስቀጠል ያስፈልጋል፡፡ የልማት ቀጣይነት ሲረጋገጥ ነው አገር እና ትውልድ ሊቀጥል የሚችለው፡፡ ‘እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል’ የሚለው አባባል፤ በእስልምና አስተምህሮ ውስጥ ቦታ የለውም፡፡”

አሁን ባለንበት ዘመን፣ በአገራችን በተለይም በአዲስ አበባ የኛ ትውልድ አካል የሆኑ “የልማት አርበኞች” ጊዜያቸውን በመስዋዕትነት በማቅረብ ትውልድ ተሻጋሪ የልማት ጡቦችን እየገነቡ መሆኑን እንመለከታለን፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በመዲናዋ ያስተዋልነው እውነታ ቢኖር “ሌሊት” የሚለው ጽንሰ-ሀሳብ መለወጡ ነው። ከተማዋ እንቅልፍ አታውቅም። እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማቶች፣ የፓርኮች ግንባታ እና የሕዝብ አገልግሎት ማሻሻያዎች አሁን ላሉበት ደረጃ የደረሱት የጊዜን አጠቃቀም ቀመር በመቀየር ነው። ቀደም ሲል በአምስት እና በስድስት ዓመታት ይከናወኑ የነበሩ ግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች አሁን ላይ በሰባት እና ስምንት ወራት ውስጥ ተጠናቀው ለአገልግሎት እየበቁ ነው። ይህ ሊሆን የቻለው የጊዜ ብክነትን በማስቀረት፣ በፈረቃ (Shift system) ሳምንቱን ሙሉ 24 ሰዓት የሰው ኃይልና ማሽነሪዎች በተቀናጀ ሁኔታ በመሰማራታቸው ነው።
ሥራን በጊዜ አለመወሰን ወይም ሥራን ቀን በጸሐይ ብቻ የማይከናወን “ኋላቀር ልማድ” በእንቅልፍ አልባዋ አዲስ አበባ ተሸንፏል ማለት ይቻላል። ቀንና ሌሊትን ለሥራ የማዋልን ባህል ቀድሞ በመተግበር የመዲናዋን ጎዳናዎች፣ ዓደባባዮች፣ ፓርኮችና ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች በማጽዳት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሙያተኞች ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አስተያየት የሰጠችን የጽዳት ሠራተኛዋ ወይዘሮ አልማዝ በቀለ፤ “አዲስ አበባን ለመቀየር ሁሉም ሰው የድርሻውን መክፈል አለበት። እኛ ሌሊት የምናጸዳው ከተማዋ ጠዋት ለዕለታዊ ኑሮ ዝግጁ እንድትሆን ነው። ሰዓታችንን ሰጥተን ከተማችንን ማሳመር ትልቅ እርካታ አለው” ትላለች።
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ምሁር የሆኑት ተስፋዬ ጮፋና (ዶ/ር)፣ አዲስ አበባ የጀመረችውን የ24 ሰዓት የሥራ ባህል ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ ጋር አያይዘው እንዲህ ሲሉ ይተነትኑታል፦“እንደ ለንደን፣ ኒውዮርክ እና ሲንጋፖር ያሉ የዓለም ታላላቅ ከተሞች የኢኮኖሚ መዋቅራቸው የተገነባው ‘Night-time Economy’ ወይም በሌሊት ኢኮኖሚ ላይ ነው። አዲስ አበባ አሁን ወደዚህ ሥርዓት እየገባች ነው። 24 ሰዓት መሥራት ማለት የከተማዋን ምርታማነት በሦስት እጥፍ ማሳደግ ማለት ነው። ይህ ደግሞ በባዶ ሜዳ የመጣ ሳይሆን፣ የሠራተኛው፣ የአመራሩና የባለሙያው ‘የጊዜና የጉልበት’ መስዋዕትነት ውጤት ነው።”
ምሁሩ አክለውም፣ ይህ ዓይነቱ የሥራ ባህል ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ ከማድረግ ባለፈ፣ የቱሪስትና የኢንቨስትመንት ፍሰቱን በማሳደግ ረገድ የላቀ ሚና እንዳለው ያስረዳሉ።
ለሰው ልጅ ከተሰጡ ውድ ጸጋዎች መካከል አንዱ የሆነው “ጊዜን” በአግባቡ መጠቀምን ይህ ትውልድ ለአገር እና ለትውልድ የሚያቀርበው መስዋዕት ሊሆን እንደሚገባ ዑስታዝ ሙሐመድ ፈረጅ ባስተላለፉት መልዕክት ፅሑፋችን እንቋጭ። “የጊዜ ባለቤት የሆነው አላህ(ፈጣሪ) ጊዜን ለበጎ ተግባር እንድንጠቀመው ነውና የሰጠን፤ ይህንን ስናደርግ ከእርሱ ዘንድ ዋጋ ያስገኝልናል፡፡ ለአገር እና ለትውልድ ዕድገት የምንችለውን ሁሉ በተሰጠን ጊዜ ውስጥ ማድረግ ግዴታ ነው፡፡ መለወጥ በማንችለው ሁኔታ ምክንያት ማድረግ የምንችለውን አለማድረግ ተገቢነትም ተቀባይነትም የለውም፡፡ ልማትን የምናለማው ራሳችንን ብቻ በማሰብ መሆን የለበትም፡፡ በልማቱ እኛ ልንጠቀም እንችላለን፣ እኛ ባንጠቀም እንኳን ልጆቻችን፣ የልጅ ልጆቻችን፣ የሰው ዘር እንዲሁም እንስሳትና አራዊት ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ዛሬ ያለንን ጊዜ ተጠቅመን የምናለማው ልማት ለሰፊ ጥቅም እንደሚውል በማመን መሆን አለበት፡፡”
በደረጀ ታደሰ