AMN የካቲት 21/2018 ዓ.ም
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ዛሬ በ4ኛ ዙር በየለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ቀን ጨልሞባቸው፣ ተስፋ ቆርጠው እና በማሕበረሰቡ ውስጥ ስር በሰደዱ ኋላ ቀር አስተሳሰቦችና ድርጊቶች ሰብዓዊ ክብራቸውን ተንጥቀው ለከፋ ማህበራዊ ችግር ተጋልጠው ይኖሩ የነበሩ 909 ሴቶችን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አሰልጥነን በማስመረቅ ወደ ስራ አሰማርተናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ላሳካልንና ላገዘን ፈጣሪ አምላክ ምስጋና ይሁን ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሰው ህይወት ላይ ለውጥ የማያመጣ ልማት የተሟላ ሊሆን አይችልም ብለዋል፡፡
አዲስ አበባችንን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባት እንዲሁም ለዘመናት የከረሙ ስብራቶቿ የሚጠገኑባት ከተማ የማድረግ ተግባራችን ጣፋጭ ፍሬ እያፈራ ነው። ለዚህም አንዱ ማሳያ የለነገዋ የሴቶች ማዕከል ዉጤት ነው።
ማዕከሉ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆነው ተስፋ ለቆረጡ እህቶቻችን አዲስ የህይወት ምዕራፍ መክፈቻ ሆኗል። ትላንት በጎዳና፣ በችግር እና በተለያዩ ማህበራዊ ቀውሶች ውስጥ የነበሩ ሴቶች ዛሬ ራሳቸውን ችለው ለተሻለ ህይወት እንዲበቁ እያስቻለ ያለ እውነተኛ የተስፋ ማዕከል ነው ብለዋል፡፡

እስከዛሬ ማዕከሉ በድምሩ 2,401 ሰልጣኞችን አስመርቆ ወደ ስራው ዓለም እንዲቀላቀሉ በማድረግ ህይወታቸውን በተሻለ መንገድ እንዲመሩና ለሌሎችም ምሳሌ እንዲሆኑ አስችሏል።
የእነዚህ የእህቶቻችን እና የልጆቻችን ህይወት ከጨለማ ወጥቶ፣ ወደ ማዕከሉ ሲመጡ የነበራቸው መልክ ተቀይሮ፣ በባህሪ ታንጸው፣ በእውቀትና በክህሎት ታጥቀው ወደ ብሩህ ነገ ሲሸጋገሩ ማየታችን የላቀ ደስታን ይሰጠናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ውድ የዘንድሮ ተመራቂዎች፤ በቆይታችሁ ካለፋችሁበት መራራ ህይወት ለመውጣት ባሳያችሁት ቁርጠኝነት እና ከፍተኛ ትጋት እንዲሁም ባሳያችሁት ፈጣን ለውጥ እጅጉን እንኮራለን። በሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምዘና (COC) 97.5 % ማስመዝገባችሁ የብቃታችሁና የትጋታችሁ ትልቅ ማሳያ ነው። ይህም በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ያሉ ሴቶች ዕድሉ ከተመቻቸላቸው፣ ትንሽ ፍቅርና ድጋፍ ካገኙ ለችግር የማይበገሩ እና ፈጣን ለውጥ የሚያመጡ መሆናቸውን በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡
አስከፊው ትላንታችሁ አልፏል፤ በማዕከሉ በነበራችሁ ቆይታ በቀሰማችሁት ክህሎት እና ባገኛችሁት የተሀድሶ ስልጠና ዛሬን ማሸነፍ ችላችኋል፤ ነገም በስራው ዓለም ለሚገጥማችሁ ማንኛውም ፈተና እጅ ሳትሰጡ ህይወታችሁን ይበልጥ ብሩህ እንደምታደርጉ አምናለሁ።
በርቱ!ውድ የማዕከሉ አመራሮች፣ የቦርድ አባላት፣ ሰራተኞች፣ በጎ ፈቃደኞች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት፤ በምድርም በሰማይም ዋጋው ከፍ ባለዉ በዚህ በጎ ተግባር ላይ ለነበራችሁ ሁለንተናዊ ተሳትፎ፣ ህይወታቸው እንዲህ በፍጥነት በተለወጠ እና “በራእይ” በተሞለው ተመራቂዎች ስም ከልብ አመሰግናለሁ ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡