የዓድዋ ድል ለአፍሪካዊያን የጋራ ደኅንነትና ወታደራዊ ትብብር ትልቅ መሠረት ነው

You are currently viewing የዓድዋ ድል ለአፍሪካዊያን የጋራ ደኅንነትና ወታደራዊ ትብብር ትልቅ መሠረት ነው

AMN የካቲት 22/2018

የዓድዋ ድል ለአፍሪካዊያን የጋራ ደኅንነትና ወታደራዊ ትብብር ትልቅ መሠረት መሆኑን የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ ገለጹ፡፡

ሁለተኛው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ኮንፈረንስ “ከአኩሪ ታሪክ፣ ወደ ብሩህ አድማስ” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

በዚህ ኮንፈረንስ የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች፣ ወታደራዊ አታሼዎችና ተመራማሪዎች እንዲሁም የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ኃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ በዚሁ ወቅት፤ የዓድዋ ድል የአፍሪካውያን የነፃነት ፋና ወጊ ከመሆኑ ባለፈ ለዛሬው አህጉራዊ ትብብር ዋነኛ መነሻ ነው፡፡

አፍሪካውያን በዓድዋ ድል የታየውን የይቻላል መንፈስ በመሰነቅ አህጉራዊ የጸጥታ እና ወታደራዊ ትብብራቸውን ይበልጥ ማጠናከር ይኖርባቸዋል ብለዋል።

መድረኩ ነገ የካቲት 23 የሚከበረውን 130ኛውን የዓድዋ ድል በዓል ታሳቢ ያደረገ ሲሆን ድሉ ለጥቁር ሕዝቦች ኩራትና ለነፃነት ተጋድሎ መነሻ መሆኑ ተናግረዋል፡፡

የሁለትዮሽና አህጉራዊ ትብብር፡ የአፍሪካ አገራት አሁን ያለውን ተለዋዋጭና ውስብስብ የዓለም የፖለቲካና የጸጥታ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ከመቼውም ጊዜ በላይ በጋራ ሊቆሙ ይገባል ብለዋል።

ድሉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ያለ ምንም ልዩነት በጋራ በመቆም ያሳኩት የቆራጥነትና የአልገዛም ባይነት ውጤት መሆኑን ጠቁመው ይህ አንድነት ዛሬም ለአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ዋስትና መሆኑን ገልጸዋል።

የዓድዋ ድል በአፍሪካና በሌሎች ዓለማት የሚገኙ ሕዝቦች ለፍትሕ፣ ለእኩልነትና ለነፃነት እንዲታገሉ መንገድ የከፈተ ታሪካዊ ገድል መሆኑን አብራርተዋል።

አገራቱ በትብብርና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ በመመስረት የጋራ ትብብር አቅም መገንባት እንዳለባቸውም መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review