AMN የካቲት 22/2018
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ወጣቱ ትዉልድ አንድነቱን በማጠናከር ፤ ሰላምን በማስጠበቅና የባህር በር ፍትሐዊ ጥያቄ ምላሽ እንዲገኝ በማድረግ ረገድ ሚናውን ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል ሲሉ ገለጹ፡፡
130ኛዉ የዓድዋ ድል “ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ“ በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ በተለያዩ ኩነቶች እየታሰበ ይገኛል፡፡
ይህዉ የአድዋ ጀግኖች ዝክረ በዓል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የሃገር መከላከያ ሰራዊት ተወካዮች፤ ወጣቶችና ሌሎች ተሳታፊዎች በተገኙበት በአድዋ ድል መታሰቢያ በፓናል ዉይይት ታስቧል፡፡

ወጣቶቹን ያወያዩት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከአድዋ ድል የምንማረው የአንድነት እና የፅናትን አይበገሬነትና አሸናፊነት ነው ብለዋል፡፡
በወቅቱ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ልዩነቶች የነበሩ ቢሆንም፣ የአድዋ ጀግኖች ግን አገር ተነካ ሲባል እንደ አንድ ልብ መካሪና እንደ አፍ አንድ ተናጋሪ ሆነው በአንድነና በጀግንነት ወራሪውን ኃይል ድል ነስተውታል ብለዋል፡፡
ይህ ትውልድም ለተግዳሮቶች ሳይበገር “አይቻልም” የሚለውን አስተሳሰብ በመቻል የቀለበሰ፣ የራሱን አንፀባራቂ ታሪክ የሰራ ፣ የታሪኩ አውራሽና ለአዳዲስ ድሎች የተዘጋጀ አሸናፊ ትውልድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ወጣቱ ትዉልድ የአድዋ ድል አደራ የሆነውን አንድነቱን በማጠናከር ፣ የኢኮኖሚ ሉአላዊነትን በማረጋገጥ ፣ ሰላምን በማስጠበቅና የባህር በር ፍትሐዊ ጥያቄ ምላሽ እንዲገኝ በማድረግ ረገድ ሚናውን ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በዉይይቱ ማረጋገጡንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡