ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለ10 ዓመታት በአልጋ ላይ ለቆየችው ሕፃን ብሌን የ4 ሚሊዮን ብር ልገሳ አደረጉ

You are currently viewing ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለ10 ዓመታት በአልጋ ላይ ለቆየችው ሕፃን ብሌን የ4 ሚሊዮን ብር ልገሳ አደረጉ

AMN- የካቲት 25/2018 ዓ.ም

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ላለፉት 10 ዓመታት በከፍተኛ የአንጎል ውስጥ ውሃ እና የአንጎል ግፊት መጨመር (ሀይድሮሴፋለስ) ምክንያት የአልጋ ቁራኛ የሆነችው ሕፃን ብሌን አሸናፊን በመኖሪያ ቤቷ ተገኝተው ጠይቀዋል።

ሕፃን ብሌን ወደ ውጭ ሀገር ሄዳ አስፈላጊውን ህክምና እንድታገኝ በሀኪሞች ቢታዘዝላትም፣ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት እስካሁን ሳይሳካላት ቆይቷል። በዛሬው ዕለት ግን ለህክምናዋ የሚያስፈልገውን 4 ሚሊዮን ብር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ልገሳ አድርገዋል።

ስጦታውን የተቀበሉት የብሌን አባት ወጣት አሸናፊ በከተማዋ በጽዳት ሰራተኝነት ተቀጥሮ እየሰራ፣ ያለእናት እርዳታ ብሌንን፣ ታናሽ እህቷን፣ ሌላኛዋን አካል ጉዳተኛ እህቱን እና በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ አገልግለው ጡረታ የወጡ አቅመ ደካማ እናቱን የሚንከባከብ፣ ለብዙዎች አርዓያ የሚሆን ጠንካራ ወጣት ሆኖ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ፣ ሕፃን ብሌን የታዘዘላትን የፊዚዮቴራፒ ህክምና እንድትከታተል በአሁኑ ወቅት የሚኖሩበት ቤት ለመቆም እንኳን የማይመችና ከህመሟ ባህሪ አንጻር እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ መገኘታቸውን ታሳቢ በማድረግ በተጨማሪም ቤተሰቡ የተሻለ መኖሪያ ቤት እንዲያገኙ የከተማ አስተዳደሩ መወሰኑን አስታውቀዋል።

በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት ይህንን በጎ ተግባር በመደገፍ፣ የብሌንን አጠቃላይ የህክምና ወጪ ለሸፈኑት ለክቡር ሼህ ሙሀመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ከልብ የመነጨ ምስጋናቸውንም አቅርበዋል።

ከንቲባ አዳነች የሕፃን ብሌን አሸናፊ ፈገግታ ተመልሶ፣ ቆማ የምትሄድበት፣ እንደ እኩዮቿ የምትቦርቅበትና ትምህርት ቤት የምትሄድበት ጊዜ ቅርብ እንዲሆን ተመኝተዋል።

በተለይም የ7 ዓመት እህቷ የማርያም አሸናፊ፣ ብሌንን ለማጫወት የምታደርገው ጥረት እጅግ ልብ የሚነካ ነው ያሉት ከንቲባዋ ፈጣሪ ልፋታቸውን ቆጥሮ እንዲክሳቸው ልባዊ ምኞታቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review