AMN – ሐምሌ 23/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ወደ ጋራ መግባባት በሚመራ መንገድ እና በመከባበር መንፈስ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት መካሄድ የጀመረው ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ፣ በራስ ችግሮች ላይ ከማተኮር ባለፈ የሌሎች ወንድምና እህቶችን ችግሮች በመረዳት እየተካሄደ ነው፡፡
የሀገራዊ ምክክሩ 4 ሺህ ተሳታፊዎች እየተመካከሩ ያሉት እንደ ሀገር ለነበሩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማስቀመጥ እና በቀጣይ በጋራ ለመኖር መፍትሔ ለማምጣት በሚያግዝ መንገድ መሆኑም ተነግሯል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ ለዘመናት የተከማቹ እና ያልተነገሩ ቅሬታዎች በግልጽ የሚወጡበት በመሆኑ፣ እየተካሄደ ባለው ጉባዔም ሐሳቦች በነፃነት ያለ ገደብ እየተነሱ ይገኛሉ፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) የውይይቱን ሂደት አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ እንደገለጹት፣ ባለፉት ቀናት ተመካካሪዎች በተመደቡባቸው ቡድኖች በተሰጧቸው አጀንዳዎች ላይ ገንቢ ውይይት አካሂደዋል፡፡
የምክክሩ ሂደት በሐሳብ ልውውጥና በጋራ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ መሆኑንም በመግለጽ፣ የአሁኑ ስልታዊ ቡድን ውይይት ከተጠናቀቀ በኋላ የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት በቀጣዩ ሳምንት 500 ተመካካሪዎችን ወደሚያሳትፈው ቀጣይ የምክክር ምዕራፍ እንደሚሸጋገርም ጠቁመዋል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ተሳታፊዎች የተወያዩባቸው ጉዳዮች እንዲሰነዱ እየተደረገ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ተሳታፊ የሚያነሳው ሐሳብ በሚገባ እንዲሰነድ ሆኖ ይቀርባል፡፡
የሻምበል ምህረት