የበርካቶችን ዕምባ ያበሱ እና ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች

You are currently viewing የበርካቶችን ዕምባ ያበሱ እና ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች

AMN – የካቲት 29/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተተገበሩ በሚገኙ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች ሴቶችን ጨምሮ በርካታ የመዲናዋ ነዋሪዎች ተጠቃሚ በመሆን ላይ ይገኛሉ፡፡

ለውጡን ተከትሎ በመዲናዋ እየተካሄዱ የሚገኙት ማዕድ የማጋራት፤ የአቅመ ደካማ ዜጎችን ቤት የማደስ ፤ የምገባ እና መሰል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች የበርካታ ነዋሪዎችን ዕምባ አብሰዋል፡፡

ከእለታዊ ምግብ ጀምሮ እስከ መኖሪያ ቤት ድረስ ድጋፍ ማግኘት የህይወት ፈተና የሆነባቸዉ በርካታ አቅመ ደካማ እና የሃገር ባለዉለታ ዜጎች ባላሰቡትና ባልገመቱት መንገድ ከከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ድጋፎችን እና ስጦታዎችን በማግኘት ላይ ይገኛሉ፡፡

በመዲናዋ እየተተገበሩ በሚገኙ የኮሪደር፤ ወንዝ ዳርቻ እና መልሶ ማልማት ስራዎች ለመኖር ምቹ ያልነበሩ አካባቢዎች በአዲስ መልክ ተገንብተዉ ለመዲናዋ አዲስ ገጽታን ያላበሱ ሲሆን በእነዚህ አካባቢዎች ሲኖሩ የነበሩ ዜጎችም ክብራቸዉን በሚመጥኑ በተሻለ መኖሪያ እና አካባቢዎች እንዲኖሩ ተደርጓል፡፡

የአቅመ ደካማ ዜጎችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ የከተማዋ ባለሃብቶች እያደረጉት ያለዉ ድጋፍና አስተዋጽኦም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መጥቷል፡፡

ከከተማ አስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየዉ ከለውጡ ወዲህ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ብቻ ከ45 ሺህ 566 በላይ ቤቶች የተገነቡ ሲሆን በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ከ4 ሺህ 990 በላይ ቤቶች ተገንብተዋል ለዜጎች ተላልፈዋል ፡፡

በእነዚህ እና መሰል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎችም የመዲናዋ ሴቶች እና እናቶች ግንባር ቀደም ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ115ኛ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለ50ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ በተከበረዉ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አሁን ላይ ሴቶች በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የብልፅግና እና የእኩልነት ጉዞ ላይ በንቃት በመሳተፍ፣ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡና የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ ብለዋል፡

ይህ ሁለንተናዊ ተሳትፎና እኩል ተጠቃሚነት በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review