ቴምርን አብዝቶ መመገብ የጤና ጉዳት እንደሚያስከትል ያውቃሉ?

You are currently viewing ቴምርን አብዝቶ መመገብ የጤና ጉዳት እንደሚያስከትል ያውቃሉ?
  • Post category:ጤና

AMN- መጋቢት 2 /2018 ዓ.ም

ቴምር የተፈጥሮ የሃይል ምንጭ ብቻ ሳይሆን ለደም ማነስ፣ ለልብ ጤና እና ለምግብ መፈጨት ስርዓት ወሳኝ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን በውስጡ የያዘ ድንቅ ፍሬ ነው።

ነገር ግን አጠቃቀሙን ካላወቅንበት ጉዳት ሊኖረው እንደሚችል ያውቃሉ?

በራስ ደስታ መታሰብያ ሆስፒታል የስርዓተ ምግብ ስፔሻሊስት ባለሙያ ሱለይማን ፍቅሬ ስለ ቴምር አስገራሚ የጤና ጥቅሞችና መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል፡፡

የቴምር የጤና ጥቅሞች

ፈጣን ጉልበት ሰጪ፣ ቴምር ከፍተኛ ካሎሪ (ግሉኮስ እና ፍሩክቶስ) ስላለው በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሰውነታችን ከፍተኛ የሃይል ምርትን ይሰጣል።

ለሆድ ድርቀትና ለጨጓራ ጤንነት፣ በውስጡ ያለው የፋይበር (Fibers) መጠን የምግብ መፈጨትን በማፋጠን የሆድ ድርቀትን ይከላከላል፤ የአንጀትና የጨጓራ ጤንነትንም ይጠብቃል።

የደም ማነስን ለመከላከል፡- ከፍተኛ የአይረን (Iron) ይዘት ስላለው ደም ማነስ እንዳይከሰት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ለልብ እና ለደም ግፊት፡- ካልሲየም እና ፖታሲየም በውስጡ በመያዙ የደም ግፊትን ለመቆጣጠርና የልብ ህመምን ለመከላከል ይረዳል።

ለአጥንት ጥንካሬ፣ ማግኒዥየም፡- ለአጥንት ጤንነት ወሳኝ የሆኑ ካልሲየም እና ፖታሲየም ማዕድናት የያዘ ነው። ለነፍሰ ጡር እናቶች፡- ነፍሰ ጡር እናቶች በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ቴምርን መመገባቸው ምጥ እንዲቀልላቸው ያደርጋል ተብሎ ይታመናል።

ምን ያህል እንጠቀም? (ጥንቃቄዎች)

ቴምር ከፍተኛ ካሎሪ ስላለው አጠቃቀማችን ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል የሚሉት ባለሙያው፣ በቀን ከሁለት እስከ ሶስት ፍሬ ብቻ መጠቀም በቂ መሆኑን ይናገራሉ።

በነዚህ ጥቂት ፍሬዎች ውስጥ ብቻ ከ500 እስከ 600 ካሎሪ ኃይል ማግኘት እንደሚቻልም ያነሳሉ። ከመጠን በላይ መጠቀም፡ ካሎሪው ከፍተኛ በመሆኑ ክብደት እንዲጨምር ወይም ለውፍረት ሊዳርግ ይችላል ብለዋል። ቴምር ከፍተኛ ጣፋጭነት ስላለው የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች ሲጠቀሙ ልዩ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review