ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከዓለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ሕብረት ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ

You are currently viewing ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከዓለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ሕብረት ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ

AMN- መጋቢት 02/2018 ዓ.ም

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከዓለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ሕብረት (ITU) ዳይሬክተር ዶ/ር ኮስማስ ዛቫዛቫ ጋር በዲጂታል ልማት ያለውን ትብብር ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት ማካሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት ኢትዮጵያ ቴሌኮምን ጨምሮ በዲጂታል መሠረተ ልማት ተደራሽነት፣ በክህሎት ልማትና በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች ተጨባጭና አስደናቂ መሆናቸውን የሕብረቱ ዳይሬክተር ገልጸውልኛል ብለዋል፡፡

የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ለዲጂታላይዜሽንና ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳችን ስላለው ፋይዳ፣ እንዲሁም በዘርፉ ስለሚኖሩ የአቅም ግንባታና አዳዲስ የትብብር ዕድሎች ሰፊ ምክክር ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ዓለም አቀፍ የመሪነት ሚና ለማሳደግና ተያያዥ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን በኢትዮጵያ በማዘጋጀት ስራዎቻችንን ለዓለም ለማስተዋወቅ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰናል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞውን ይበልጥ ለማፋጠንና የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ከግብ ለማድረስ ITU ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚያደርግም ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

በቀጣይም በጀመርናቸውና በሌሎች አዳዲስ ዘርፎች ዙሪያ በጋራ በመስራት የሀገራችንን ዲጂታል ልማት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር ጽኑ ዝግጁነት ተፈጥሯል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በመልዕክታቸው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review