ባለፉት ሳምንታት የተደረጉ የመሪዎች ጉብኝቶች የኢትዮያን የትብብር አጋርነት ተመራጭነት የሚያጎሉ ናቸው

You are currently viewing ባለፉት ሳምንታት የተደረጉ የመሪዎች ጉብኝቶች የኢትዮያን የትብብር አጋርነት ተመራጭነት የሚያጎሉ ናቸው

AMN-ሚያዝያ 22/2018 ዓ.ም

ባለፉት ሳምንታት በኢትዮጵያ የተደረጉ የመሪዎችና የሀገራት ከፍተኛ ልዑካን ይፋዊ ጉብኝቶች የኢትዮያን የትብብር አጋርነት ተመራጭነት የሚያጎሉ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

ባለፋት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ብቻ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት፣ የሞዛምቢክ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ዳንዔል ፍራንሲስኮ ቻፖ፣ የላይቤሪያ ፕሬዝደንት ጆሴፍ ቦአካይ እንዲሁም የብሩንዲ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ኤቫሬስቲየ ኒዲያየሽሚየ እና የአውሮፓ ኅብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጆሴፍ ሲከላ በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ማድረጋቸውን ቃል አቀባዩ አውስተዋል።

የፖርቹጋል፣ የኦስትሪያና ባንግላዴሽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም የሰሞኑ የአዲስ አበባ እንግዶች ነበሩ። ይህም የኢትዮጵያን ለአጋርነት አብዝቶ መፈለግን የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ከነዚሁ ልዑካን ጋር ባደረጓቸው ምክክሮችም በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የትብብር መስኮች ጠንካራና የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስምምነቶች የተደረሱባቸው እንደነበሩ አምባሳደር ነብያት ተናግረዋል።

ባለፉት ሳምንታት በአዲስ አበባ የተካሄዱ የኢትዮ- አውሮፓ ህብረት እንዲሁም የኢትዮ- ቼክ ሪፐብሊክ የቢዝነስ ፎረሞች ኢኮኖሚያዊ አበርክቷቸው ጉልህ እንደነበርም አንስተዋል።

ጉብኝቱን ተከትሎ የተካሄዱ ምክክሮች ሀገራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ አዳዲስ አጋርነቶችንም ማስገኘት ያስቻሉ ስለመሆናቸውም አክለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ኢትዮጵያ የዓለምን ምጣኔ ሀብት እያወከ ያለው የሆርሙዝ ወሽመጥ ቀውስ በሰላማዊ የንግግር መፍትሄ እንዲፈታ ጥረቷን አጠናክራ መቀጠሏን አምባሳደር ነብያት አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ለአንድ ወር በሊቀመንበርነት እያገለገለች ባለው የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት የሆርሙዝ ቀውስ አጀንዳ ዘላቂ መፍትሄ እንዲበጅለትም ጥሪ ማቅረቧን አስታውቀዋል።

በአቡ ቻሌ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review