AMN- መጋቢት 8/2018 ዓ.ም
መንግሥት ሁሉንም የሃይማኖት ተቋማት በእኩልነት እንደ ዕሴቶቻቸውና አስተምህሯቸው በፍትሃዊነት ያገለግላል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
ከሌሎች የሀይማኖት ተቋማት ጋር እንዳደረግነው ሁሉ ዛሬ ከኢትዮጵያ ወንጌላውያን፣ ከካቶሊክ እና ከሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያናት መሪዎች ጋር “የሃይማኖት ተቋማት በመደመር መንግሥት እይታ” በሚል መሪ ሀሳብ ፍሬያማ ውይይት አካሂደናል ብለዋል።
ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት፣ የካቶሊክ እና የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን በሰላም፣ በልማትና በትውልድ ግንባታ ሂደት ውስጥ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲዳብር፣ አንድነት እንዲጠነክር፣ ትውልድ እንዲማር፣ በስነምግባር እንዲታነፅ፣ ታሪክንና ቅርስን በመጠበቅ እንዲሁም ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና አበርክተዋል ሲሉ በውይይቱ አብራርተዋል።

በተጨማሪም ቴክኖሎጂን ወደ ሀገር በማስገባትና የሥራ ባሕልን በማበረታታት ረገድ ከሌሎች የሀይማኖት ተቋማት ጋር በመሆን ወሳኝ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በታሪክ ብቻ ሳይሆን ባለፉት የለውጥ ዓመታትም ተቋማቱ በከተማችን ሁለንተናዊ የሰላም ግንባታ፣ የልማት እና የብልጽግና ጉዞ ላይ እያበረከቱት ያለው ተሳትፎ ጉልህ መሆኑንም አንስተዋል።
በመድረኩ ለሕዝቦች ትስስር መጎልበት፣ በማኅበራዊ ልማትና በበጎ ፈቃድ ሥራዎች ተሳትፎ፣ የሥራ ባሕልን በማስረጽ፣ ትውልድን በሥነ ምግባር በመገንባት፣ የበጎነት ስራ መስራት እንዲለመድ በማድረግ፣ ለመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ መጎልበት እንዲሁም ሰላምን በማስፈንና ሕገወጥነትን በመከላከል ረገድ ለኢትዮጵያ ብልጽግና እና ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ ለመቆም ጠቃሚ ውይይት አድርገናል ብለዋል።

ከንቲባዋ አክለውም በውይይታችን የተነሱ በስራ ሂደት ያጋጠሙ አንዳንድ ክፍተቶችን እና እንግልቶችን በቀጣይ በትብብር ለማረም የሚያስችል ምቹ መደላድል የፈጠረ ውጤታማ መድረክም ነበር ብለዋል።
ይህ መድረክ በየክፍለ ከተማው ሲካሄዱ የቆዩ ውይይቶች ማጠቃለያ ሲሆን፣ የመንግሥትንና የሃይማኖት ተቋማትን ሚና እና ድርሻ በግልጽ ለይቶ ያስቀመጠ ነው።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ የወንጌላውያን ፣ የካቶሊክ እና የኢትዮጵያ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን መሪዎች ላደረጉት ከፍተኛ ተሳትፎና ለሰጡት ገንቢ ሐሳብም በከተማ አስተዳደሩ ስም ምስጋና አቅርበዋል።