የአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ችግኞችን በመትከል የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል

You are currently viewing የአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ችግኞችን በመትከል የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል

AMN- ሐምሌ 26/2018 ዓ.ም

የአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ከማለዳው ጀምሮ ችግኞችን በመትከል የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የሐይማኖት ተቋማት አስታወቁ፡፡

ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር ቆይታ ያደረጉ የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች፤ በነገው ዕለት የሚከናወነው የአንድ ጀንበር 800 ሚሊየን ችግኝ የመትከል ሀገራዊ ዕቅድ እንዲሳካ የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መላከ ምህረት ቆሞስ አባ ገ/መድህን ንጉሴ፤ የተራቆተችዋን ምድር ጸጋንና ልምላሜን ለማልበስ ኢትዮጵያውያን ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸው የሚያስደንቅ ነው ብለዋል፡፡

መርሐ ግብሩ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እያደገ እና ዓለምን እያስደመመ ያለ መልካም ተግባር በመሆኑ ምእመናን በችግኝ ተከላው ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳይ ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሱልጣን ሃጂ አማን ኤባ በበኩላቸው፤ ለነገው ትውልድ የለማች ሃገር ለማስረከብ መርሃ ግብሩ ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ ለዚህም ችግኞችን እንድንተክል ህሊናችን ያዘናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

መርሐ ግብሩ ህዝብንም ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ሁሉም ፆታ፣ ዕድሜና የኑሮ ደረጃ ሳይለየው ከማለዳው ጀምሮ ችግኞችን በመትከል የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

ተፈጥሮን መንከባከብና መጠበቅ ከመንፈሳዊ አስተምህሮት ጋር ቁርኝት ያለው መልካም ተግባር መሆኑን ያነሱት ደግሞ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ጸሃፊ መጋቢ ጌትነት ለማ ናቸው፡፡

በዚህም የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ምእመናንን በማስተባበር በመርሃ ግብሩ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ሁሉም ዜጋ ነገ በሚከናወነው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በንቃት እንዲሳተፍም የሐይማኖት አባቶች ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review