AMN – ሐምሌ 26/ 2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ማዕቀፍ ውስጥ ሌላ ታሪካዊ ምዕራፍ ለማስመዝገብ ተዘጋጅታለች። በመላ ሀገሪቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በመሳተፍ በአንድ ቀን 800 ሚሊዮን ችግኞችን ሊተክሉ ማለዳን እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ፣ 48 የፌዴራል ተቋማት በሀገር አቀፉ የችግኝ ተከላ ዘመቻ እንዲሳተፉ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የተከላ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን አስታውቋል።
ተቋማቱ የሚተክሉባቸው ሥፍራዎች እና የሚተክሏቸው ችግኞች ብዛት ድልደላ ተከናውኗል፡፡
በአጠቃላይ የፌደራል ተቋማቱ 260ሺ 700 ችግኞችን በመዲናዋ የተለያዩ ቦታዎች እንዲተክሉ እንደተዘጋጀላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
በአዲስ አበባ በአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል ሙሉ ዝግጅት ተደርጓል፡፡
በ2011ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር ) አመራር የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ ከአፍሪካ ትልቁ የአካባቢ መልሶ ማቋቋም መርሃ ግብሮች መካከል አንዱ ሆኗል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ 8 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል እንቅስቃሴ ላይ ያለችው ኢትዮጵያ፣ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ሌላ አዲስ ታሪካዊ ክብረ ወሰን በማስመዝገብ ለአካባቢ ጥበቃ ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት ዳግም እንደምታረጋግጥ ይጠበቃል።
በብርሃኑ ወርቅነህ