ልጆች፤ በዒድ አልፈጥር ስለሚደረግ የቤተሰብ ጥየቃ ምን ያህል ታውቃላችሁ?

You are currently viewing ልጆች፤ በዒድ አልፈጥር ስለሚደረግ የቤተሰብ ጥየቃ ምን ያህል ታውቃላችሁ?

ልጆች፤ እንዴት ናችሁ? በየዕትሙ ለእናንተ የምናዘጋጃቸውን ጽሑፎች እያነበባችሁና እርስ በእርስ ሀሳብ እየተለዋወጣችሁ ነው የሚል እምነት አለን፡፡ ጎበዝ ልጆች፡፡ ዛሬ ደግሞ የዒድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ቤተሰብን ስለመዘየር (ስለመጠየቅ) መረጃ እናጋራችኋለን፡፡ ለዚህ ደግሞ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ ልጆችና የኃይማኖት አባት ለዝግጅት ክፍላችን የሰጡትን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ 

ኢክራም አህመድ እባላለሁ፡፡ በበዓል ዕለት የተገዛልኝን አልባሳትና ጫማ በመልበስ ዘመዶቼን ለመዘየር  እሄዳለሁ። ሁልጊዜ በዓል ሲመጣ ወደ አክስቶቼ ቤት እሄዳለሁ፡፡ የእድሜ እኩዮቼንም በጣም ናፍቀውኝ ስለማገኛቸው በዓሉን በጉጉት ነው የምጠብቀው፡፡ እርስ በእርሳችን በስፍራው ላይ ስንገናኝ ፍቅር እንሰጣጣለን፡፡ ታላላቆቻችንም በዕለቱ ይመርቁናል፤ ዱአም ያደርጉልናል፡፡

ሂዳያ ፈድሉ እባላለሁ፡፡ ለበዓል ቤተሰብን የመዘየር ልምድ አለኝ፡፡ በአካል ማግኘት የማንችላቸውን ዘመዶቻችንን በስልክ የማገኛቸው ሲሆን ጎረቤቶቻችንን ደግሞ ሄጄ እዘይራቸዋለን፡፡ ስንዘይር ታድያ የሚበሉ ጣፋጭ ኬኮችንና ፍራፍሬዎችን በመያዝ ጭምር ነው፡፡

ከጎረቤት ጋር መጠያየቅ እንዲሁም የሩቅ ዘመዶችን ማስታወስ እንደሚገባ ሁልጊዜ እናትና አባቴ ይነግሩኛል፡፡ እኔም ለመጠየቅ በምንሄድበት ጊዜ ጓደኞቼን በመጠየቅ ይኸን ለማድረግ እሞክራለሁ፡፡

መሀመድ አንዋር እባላለሁ፡፡ በዓል በመጣ ቁጥር የምናፍቀው ነገር ቢኖር የቆዩ ቤተሰቦቼን አግኝቶ መዘየር ነው፡፡ አያቴና አክስቴ በጣም ስለሚናፍቁኝና ሁልጊዜ አብሬያቸው ብሆን ብዬ ስለምመኝ የበዓል ቀኑን በጣም እናፍቀዋለሁ፡፡ እነሱም የሚያሳዩኝ ፍቅር ሁሌም እንድናፍቃቸው ያደርገኛል፡፡ ደስ በሚለው በበዓል ቀን ደስታችንን ለመካፈል እንደ ቤተሰብ መሰባሰብ እና መዘያየር የተለየ ድባብ  እና ከፍተኛ የደስታ ስሜት አለው፡፡

ሼህ ማህሙድ ኢብራሂም እባላለሁ። በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 አንሷር መስጂድ ዋና ኢማም ነኝ፡፡ ልጆች፤ መዘየር ማለት ለመልካም ነገር ጉብኝት ማድረግ ማለትን ይወክላል፡፡እንደ እስልምና ኃይማኖት ለመልካም ነገር ሰዎችን መጠየቅ በፈጣሪ ዘንድ ጥቅም ያስገኛል፡፡ ልጆች እናት፣ አባት፣ አጎት፣ አክስት፣ ወንድም፣ እህት፣ አያቶች እንዲሁም ቅርብ የሆኑ ሰዎች ጋር በመሄድ የመዘየር ሂደት ይከናወናል፡፡ አዲስ ልብስ ለብሳችሁ የናፈቋችሁን ወዳጆች በዚያ ዕለት ማግኘት ስሜቱ እጅግ የሚያስደስት ነው ፡፡

የመዘየር ጠቀሜታው ደግሞ እርስ በእርስ ዝምድናችሁን እንድታጠናክሩ ያግዛል፡፡ በቅዱስ ቁራን ላይ እንደተፃፈው “ሰዎች ሆይ የፈጠራችሁን አምላካችሁን ፍሩ፤ ታዘዙ፡፡ ዝምድናውን መቀጠል እንደሚጋባም በቁራን ላይ በግልፅ ተቀምጧል።” ታላላቆቻችንን ስንዘይራቸው የሚሰማቸው ደስታ ይህ ነው ተብሎ አይገለፅም፡፡ በምላሹም ፀሎት ይደረጋል፤ ምርቃትም ይሰጣል፡፡ ይህ ደግሞ ቀጣይ ለሚኖራችሁ የሕይወት ቆይታ መሠረት ይጥላል፡፡ በታላላቆቹ የተመረቀ ልጅ ስኬታማ እና በፈጣሪ ዘንድ የተወደደ እንዲሆን ያደርጋል፡፡

ልጆች ከዚህ ስርዓት የምትማሩት እንዴት ማህበራዊ ህይወታችሁን መምራት እንደምትችሉ ነው፡፡ ከታላላቆቻችሁ ጋር ስትገናኙ የሚሰጧችሁን ምክረ ሀሳቦች መተግበር ይኖርባችኋል፡፡ በፍፁም ትዕግስትና ሥነ ምግባር ውስጥ ራሳችሁን ማግኘት ይጠበቅባችኋል፡፡ ይህ ደግሞ ለተቀረው የሕይወት ዘመናችሁ ስንቅ ይሆናችኋል፡፡ ለጥየቃ በምትሄዱበት ወቅት ቢቻል የኑሮ ጫና ውስጥ ላለ ሰው ጠቃሚ ነገሮችን ይዞ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በእጦት ዙሪያ ችግር የሌለባቸው ዘመዶች ጋር ከሆነ የምትሄዱት ኬክ፣ ፍራፍሬ እና መሰል ነገሮችን ይዛችሁ መሄድ ትችላላችሁ፡፡

በሄለን ጥላሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review