ደኖች የዓለማችን ሳንባዎች ናቸው

You are currently viewing ደኖች የዓለማችን ሳንባዎች ናቸው

AMN- መጋቢት 12/2018 ዓ.ም

ደኖች የምድራችን ሳንባዎች ሲሆኑ፣ የዛሬው ዕለትም መጋቢት 12 የዓለም የደን ቀን ሆኖ እየተከበረ ይገኛል።

ዓለማችን በደን መጨፍጨፍ ሳቢያ በየዓመቱ 4.5 ትሪሊየን ዶላር የሚገመት ሀብት እንደምታጣ የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት ጥናት ያመላክታል።

ለምን ትኩረት እንስጥ?

የአየር ንብረት ጠባቂ፦ ደኖች በየዓመቱ 2.6 ቢሊየን ቶን ካርቦንዳይኦክሳይድን በመምጠጥ የምድር ሙቀት እንዳይጨምር ያደርጋሉ። የሕይወት መገኛ፦ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የየብስ እንስሳትና ዕፅዋት መኖሪያቸው ደን ነው።

በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ40 ቢሊየን የተሻገሩ ችግኞችን በመትከል የተራቆቱ ደኖችን እንዲያገግሙ የነጠፉ ሐይቆች ወደ ተፈጥሯቸው እንዲመለሱ ከማድረግ ባሻገር የከባቢ አየር ብክለትን በመከላከል ረገድ ውጤታማ ሥራ በመሠራቱ በአህጉር እና በዓለም አቀፍ መድረክ ሥራው ዕውቅና ማግኘት መቻሉን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

እንደ መንግሥት ይፋዊ መረጃዎች እና እንደ ግብርና ሚኒስቴር ሪፖርቶች፣ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን አሁን ላይ ከ17.3 ወደ 23.6 በመቶ ከፍ ብሏል።

በአዲስ አበባ የታየው የአረንጓዴ ልማት ሥራ እንደ እንጦጦ ፓርክ፣ ወዳጅነት ፓርክ፣ እና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች እንዲሁም የወንዝ ዳርቻ ልማት የከተማዋን የደን ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጎታል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ የተቀናጀ የደን ልማት ሥራ በመሠራቱ የደን ጭፍጨፋን በአማካይ ከ92 ሺህ ሄክታር ወደ 27 ሺህ ሄክታር መሬት ዝቅ ማድረግ መቻሉን የኢትዮጵያ ደን ልማት መረጃ ያሳያል፡፡

በዓለማችን የደን ሀብት ከ1.6 ቢሊየን በላይ ለሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የኑሮ መሠረት መሆኑንና ለምግብ ዋስትና፣ ለመድሃኒት ግብዓትነት እና ለገቢ ምንጭነት ደኖች ሚናቸው የጎላ መሆኑንም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review