AMN- ሐምሌ 10/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሚል የጀመረችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ የሀገሪቱን ምጣኔ- ሀብታዊ መዋቅር በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
መርሐ ግብሩ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የኢኮ-ቱሪዝም ዘርፍን በማነቃቃት እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ትልቅ የኢኮኖሚ ምሰሶ እየሆነ መምጣቱ ይታወቃል።
እንዲሁም የአፈር መሸርሸርን መከላከል እና የከርሰ-ምድር ውሃን ማበልጸግ ከአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ትሩፋት ውስጥ ተጠቃሽ ሲሆኑ ለግብርናው ዘርፍ መነቃቃትም ትልቅ አቅም ፈጥሯል፡፡
በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ትኩረት የተሰጠው የፍራፍሬ እና ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸው የአርሶ አደሩን የገቢ ምንጭ ከማሳደጉም በላይ የሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ለማሟላት አስችሏል።

የአቮካዶ፣ የማንጎ፣ የፓፓያ እና የቡና ምርቶች በስፋት መመረታቸው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶችን በማሳደግ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ሲሆን ይህም ግብርናው ከተለመደው አሠራር ወጥቶ ከፍተኛ የገበያ ዋጋ ያላቸው ምርቶች እንዲመረቱ በር ከፍቷል።
በየዓመቱ በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን በማዘጋጀት፣ በመትከል እና በመንከባከብ ሂደት ውስጥ በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች እና ሴቶች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።
ከችግኝ ጣቢያዎች ዝግጅት ጀምሮ እስከ ደን ልማት ጥበቃ ድረስ ያለው ሰንሰለት በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ አድርጓል።

ከዚህ በተጨማሪም በከተሞች የተገነቡት ዘመናዊ መናፈሻዎች እንዲሁም ፓርኮች ለሀገር ውስጥና ለውጭ ቱሪስቶች መዳረሻ በመሆን የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን በማነቃቃት ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ይገኛል፡፡
ይሄም የከተማ ውበትን ከመፍጠር ባለፈ በቱሪዝምና መስተንግዶ ዘርፍ ውስጥ ሰፊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲፈጠር እና የሀገር ገጽታ እንዲገነባም አድርጓል።
አረንጓዴ ልማት ለአሁኑ ትውልድ የምግብ ዋስትና ከመሆን ባለፈ ወደፊት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የካርቦን ሽያጭ ገበያ ላይ እንድትሳተፍ እና ከዓለም አቀፍ አረንጓዴ ፈንድ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችል ትልቅ መዋዕለ-ነዋይ መሆኑን የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
ኢትዮጵያ የደን ሽፋኗን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሳደግ መቻሏ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኘውን አረንጓዴ ፋይናንስ እና የካርቦን ሽያጭ ገበያን ለመቀላቀል ሰፊ ዕድል ከፍቶላታል።

በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችን አስቀድሞ በመከላከል ረገድ የሚድነውን የሀገር ሀብት ሳይጨምር የተፈጠረው ለምለም አካባቢ የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ዋስትናን የሚያረጋግጥ ነው።
የአረንጓዴ ዐሻራ ትሩፋቶች ለአሁኑ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድም አስተማማኝ ምጣኔ-ሀብታዊ መሰረት የሚጥሉ ነው፡፡
በወርቅነህ አቢዮ