የኒኮ ኦሪሊ ድንቅ ምሽት እና የኬፓ ከባድ ስህተት

You are currently viewing የኒኮ ኦሪሊ ድንቅ ምሽት እና የኬፓ ከባድ ስህተት

AMN- መጋቢት 15/2018 ዓ.ም

ማንቸስተር ሲቲ የ2026ቱን የካራባኦ ካፕ ዋንጫ ሲያነሳ፤ አርሰናል በግለሰብ ስህተቶች ዋጋ ከፍሏል፡፡

በታሪካዊው ዌምብሌይ ስታዲየም በተካሄደው የካራቦኦ ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ፣ ማንቸስተር ሲቲ አርሰናልን 2-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የዘንድሮውን ዋንጫ ማንሳት ችሏል።

ይህ የፔፕ ጓርዲዮላ ስብስብ በውድድሩ ታሪክ ለ9ኛ ጊዜ ዋንጫውን ሲያነሳ፣ የ21 ዓመቱ ወጣት ኒኮ ኦሪሊ እና የአርሰናሉ ግብ ጠባቂ ኬፓ አሪዛባላጋ የጨዋታው ዋነኛ መነጋገሪያ ሆነዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ ፉክክር አሳይተው ያለ ግብ ቢጠናቀቅም፣ በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል።

በ60ኛው ደቂቃ ላይ ራያን ቼርኪ ያሻገረውን ኳስ የአርሰናሉ ግብ ጠባቂ ኬፓ አሪዛባላጋ በአግባቡ መቆጣጠር ባለመቻሉ፣ 21ኛ ዓመት የልደት በዓሉን በማክበር ላይ የነበረው ኒኮ ኦሪሊ በግንባሩ በመግጨት ሲቲን መሪ አድርጓል።

ከ4 ደቂቃዎች በኋላ በ64ኛው ደቂቃ ማቲየስ ኑኔዝ ያሻገረለትን ኳስ ኦሪሊ በድጋሚ በግንባሩ በማስቆጠር የማንቸስተር ሲቲን አሸናፊነት አረጋግጧል።

የውድድር ዘመኑን ምርጥ ብቃት እያሳየ የሚገኘውን ዴቪድ ራያን በማስቀመጥ ኬፓን በቋሚነት ማሰለፍ “ትልቅ ስህተት” ተብሎ በብዙዎች ቢተችም፣ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ግን ውሳኔያቸውን በጽኑ ተከላክለዋል።

እንደ ፎክስ ስፖርትና ቢቢሲ ዘገባ፤ አርቴታ ከጨዋታው በኋላ በሰጡት መግለጫ፣ “ኬፓ በውድድሩ ላይ እስካሁን ጥሩ ሲያገለግለን ቆይቷል፤ እሱን አለማሰለፍ ፍትሃዊ አይሆንም ነበር” ብለዋል።

አክለውም “ሽንፈቱ እጅግ በጣም ያማል፤ ነገር ግን ይህንን ህመም በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ለሚጠብቁን ጨዋታዎች እንደ ነዳጅ እንጠቀምበታለን” በማለት ተጫዋቾቻቸው ትኩረታቸውን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እና ሻምፒዮንስ ሊጉ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

አርሰናል በመጀመሪያዎቹ የጨዋታ ደቂቃዎች ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርቦ ነበር። በ7ኛው ደቂቃ ላይ ካይ ሃቨርትዝ እና ቡካዮ ሳካ በተከታታይ ያደረጓቸውን ሶስት አደገኛ ሙከራዎች የማንቸስተር ሲቲው ተጠባባቂ ግብ ጠባቂ ጀምስ ትራፎርድ በሚያስደንቅ ሁኔታ በማዳን ቡድኑን በጨዋታው ውስጥ አቆይቷል።

ስቢኤስ ስፖርትስ እንደዘገበው ሪካርዶ ካላፊዮሪ በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ ሁለት ጥሩ ሙከራዎችን ቢያደርግም የጨዋታውን ውጤት መቀየር አልቻለም።

ይህ ድል ፔፕ ጓርዲዮላን በካራበኦ ካፕ ታሪክ 5 ዋንጫዎችን በማንሳት ውድድሩን በበላይነት የመሩ አሰልጣኝ አድርጓቸዋል። ማንቸስተር ሲቲም በውድድሩ 9ኛ ዋንጫውን በማንሳት ከሊቨርፑል 10 ዋንጫዎች ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

እንደ ዘጋርዲያን ዘገባ ይህ ሽንፈት አርሰናል በዘንድሮው የውድድር ዘመን አራት ዋንጫዎችን ለማንሳት የነበረውን ህልም ያጨለመ ቢሆንም፣ ቡድኑ አሁንም ፕሪሚየር ሊጉን በመምራት ላይ ይገኛል፤ እንዲሁም በሻምፒዮንስ ሊጉ ሩብ ፍጻሜ ከስፖርቲንግ ሊዝበን ጋር እና በኤፍ ኤ ካፕ ሩብ ፍጻሜ ከሳውዝሃምፕተን ጋር ወሳኝ ጨዋታዎች ይጠብቁታል።

በአጠቃላይ ጨዋታው ማንቸስተር ሲቲዎች አሁንም በዋንጫ ጨዋታዎች ያላቸውን ልምድ ያሳዩበት ሲሆን፣ አርሰናል ደግሞ ያልታሰቡ የግለሰብ ስህተቶች ዋጋ እንዳስከፈሉት የዓለም ሚዲያዎች እየዘገቡ ይገኛሉ።

ፔፕ ጓርዲዮላ ከድሉ በኋላ፤ “ሚኬል አርቴታ ፈጽሞ የማይበገር ቡድን ነው የገነባው። አርሰናል ከባየር ሙኒክ እና ባርሴሎና ጋር በአውሮፓ ውስጥ ካሉ ምርጥ ቡድኖች አንዱ ነው። ይህንን የመሰለ ጠንካራ ቡድን አሸንፎ ዋንጫ ማንሳት ድሉን ልዩ ያደርገዋል” በማለት የአርቴታን ስብስብ አድንቋል።

ሚኬል አርቴታ ከሽንፈቱ በኋላ በጣም እንዳዘኑና፣ ለመቀበል እጅግ እንደከበዳቸው፤ በተለይም ለተጫዋቾቻቸው እና ለደጋፊዎቻቸው ይህ ዋንጫ ምን ያህል ትርጉም እንዳለው እና ምን ያህል ይፈልጉ እንደነበር በመግልጽ በመጨረሻም ማሳካት አለመቻላቸው መጥፎ ስሜት ጥሎባቸው ማለፉን በምሬት ተናገርዋል፡፡

በቶለሳ መብራቴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review