AMN -መጋቢት 17/2018 ዓ.ም
ታዋቂዉ እና ዝነኛዉ ጥቁር አሜሪካዊዉ ራፐር እና ዩቲዩበር ዳረል ድዌይን ግራንቤሪ ጁኒየር (ዲዲጂ) አዲስ አበባን በመጎብኘት ላይ ይገኛል፡፡
ዲዲጂ በዋናነት ራፐር እና ዩቲዩበር ሲሆን፣ ጥበብንና ኢንተርኔትን አጣምሮ በመያዝ በዓለም ላይ ስኬታማ የሆነ ወጣት ነው። ዲዲጂ እ.ኤ.አ ጥቅምት 10 ቀን 1997 ፖንቲያክ፣ ሚቺጋን ተወለደ፡፡ ዲዲጂ መጀመሪያ የታወቀው በዩቲዩብ ቪዲዮዎቹ ነው።
በዩኒቨርሲቲ ተማሪነቱ ወቅት ቪዲዮዎችን መስራት የጀመረ ሲሆን፣ በኋላም ትምህርቱን አቋርጦ ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ስራው ገብቷል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮችም አሉት።
ወጣቱ ራፐር እና ዩቲዩበር ዲዲጂ የራሱን የሙዚቃ ሌብል በማቋቋም ንቁ የንግድ እንቅስቃሴ በማድግ ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ዲዲጂ ከዩቲዩብ ወደ ሙዚቃው ዓለም በተሳካ ሁኔታ ከተሻገሩ ጥቂት የዓለማችን ታዋቂ ሰዎች አንዱ ነዉ፡፡

በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በጣም ንቁ ሲሆን፣ ብዙ ጊዜ የራሱን የቅንጦት ህይወትና የግል እንቅስቃሴዎቹን ለደጋፊዎቹ በማጋራት ይታወቃል፡፡
ይህ ጥቁር አሜሪካዊ ራፐር እና ዩቲዩበር የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጨምሮ በአዲስ አበባ በተለያዩ አካቢዎች ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
በኮሪደር እና ወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች አዲስ ገጽታን የተላበሰቸዉ አዲስ አበባ ከቅርብ አመታት ወዲህ በዓለም ላይ ታዋቂ በሆኑ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪዎች፣ በመሪዎች፣ በአርቲስቶች፣ ሙዚቀኞችና በታዋቂ ሰዎች በተደጋጋሚ እየተጎበኘች ትገኛለች፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ