በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች የሚፈልጉትን ፓርቲ በነፃነት መምረጥ መቻላቸውን ታዝበናል – ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች

AMN – ግንቦት 25/2018 ዓ.ም

ትላንት የተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ ፣ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ንቁ ክትትል ተካሄዷል።

በምርጫው ዕለት የሀገር ውስጥ የሲቪል ማህበራት ጥምረትን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት እና የኢጋድ ታዛቢ ቡድኖች በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ሂደቱን ተመልክተዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪና የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ዜጎች ያለምንም ጫና የሚፈልጉትን ፓርቲ በነፃነትና በሙሉ ፈቃዳቸው መምረጥ መቻላቸውን ታዝብናል ሲሉ ገልጸዋል።

ኡሁሩ ኬንያታ አክለውም፣ በኢትዮጵያ የታየው የምርጫ ሂደት ለመላው አፍሪካ ትልቅ ትርጉም እንዳለውና በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ምሳሌ መሆን የሚችል መሆኑን አስገንዝበዋል።

በተመሳሳይ በዶክተር ስፔሲዮዛ ዋንዲራ-ካዚብዌ የሚመራው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ታዛቢ ቡድን የምርጫውን ሂደትና የህዝቡን ከፍተኛ ተሳትፎ አድንቋል።

የቡድኑ መሪ በተለይ የሴቶች፣ የወጣቶች፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ መጎልበቱን የጠቀሱ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ወጣቶች በቴክኖሎጂ እና በምርጫ ክትትል ሂደቶች ላይ ያሳዩት ተሳትፎ በአፍሪካ የዲሞክራሲ ጉዞ ውስጥ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በምርጫ ሂደት ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከብዙ የአፍሪካ ሀገራት ቀድማ መገኘቷ መረጃዎች በፍጥነት እንዲደርሱና ለሚፈጠሩ ጥቃቅን ችግሮች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ማገዙን ቡድኑ ጠቁሟል።

ሁለቱም የታዛቢ ቡድኖች የመጀመሪያ ደረጃ ሙሉ ግምገማቸውን ይፋ ከማድረጋቸው በፊት፣ የድምፅ ቆጠራና የውጤት ማጠቃለያ ሂደቶችን በቅርበት እየተከታተሉ ይገኛል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ህብረት 3 ሺህ 149 ታዛቢዎችን በማሰማራት፣ 2 ሺህ 258 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ላይ ሂደቱን በንቃት በመከታተል ለምርጫው ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review