AMN ሰኔ 10/2018 ዓ.ም

በጎ ፈቃደኝነት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የሰብዓዊነት ተግባር ነው፡፡
በከተማችን የክረምትና የበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፕሮግራሞች ተቀርጸው በጎ ፍቃደኛ ባለሃብቶች፤ ወጣቶችንና መላው የከተማችን ነዋሪዎች ለከተማቸው በበጎነት ጉልበታቸውን፤ ገንዘባቸውን፣ ጊዜያቸውንና እውቀታቸውን እንዲያበረክቱ በማድረግ ለማህበረሰቡ በተደራጀ መንገድ የተለያዩ የሰብዓዊነት አገልግሎቶችን በመሰጠት ይገኛል፡፡

በጎ ፈቃደኝነት በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ሁኔታ በሚፈጠር ችግር፣ በፈተና እና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ግንባር ቀደሞ ደራሽ መሆን ነው፡፡ “ሁሉም ቢረዳዳ ሁሉም ቢተባበር የት ይደረስ ነበር” ሁሉም ሰው በጎ ፈቃደኝነት ቢያዘወትር ዓለም ለሰው ልጅ ሁሉ የተሻለ ምቹ ትሆን ነበር የሚባለው ለዚህ ሳይሆን አይቀርም።

ባለፉት ዓመታት በአዲስ አበባ ተቀርፀው በተከናወኑ ከ15 በላይ ዋና ዋና አሳታፊ የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብሮች፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህልና ተደራሽነት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መጥቷል።

በእነዚህ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ከ55.7 ቢሊዮን ብር በላይ የበጎ ፍቃድ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በየዓመቱ በአማካይ ከ2.6 ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ፣ በድግግሞሽ 9.3 ሚሊዮን የሚሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
በከተማችን ከተከናወኑ መጠነ ሰፊ የበጎ ፈቃድ ስራዎች መካከልም በቤት ግንባታ መርሀ ግብር 46ሺህ 441 ቤቶች ተገንብተው ለአቅመ ደካሞችና ለሀገር ባለውለታዎች ተላልፈዋል። በድግግሞሽ 6.1 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ማዕድ ተጋርተዋል፡፡በህፃናት ድጋፍ መርሀ ግብር ወላጆቻቸውን ያጡ 2 ሺህ 351 ህፃናት የልዩ ድጋፍ ተጠቃሚ ሆነዋል። ከፍለው መታከም የማይችሉ 525ሺህ 531 ወገኖች ነጻ የህክምና አገልግሎት ያገኙ ሲሆን 354,938 ዩኒት ደም በበጎ ፈቃደኞች ተለግሷል።ለ632 ሺህ 497 ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርትና የስልጠና ድጋፍ ተደራሽ ሆኗል።
በየዓመቱ ከ20 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች በመንገድ ትራፊክ ደህንነት፣ በሙያ በጎ ፈቃድ መርሃ ግብሮች ላይ ተሳትፈዋል፡፡
የበጎ ፈቃድ ፕሮግራም በከተማችን የነበረውን የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴት ከማሳደጉም በላይ፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎች አለኝታ መሆን የቻለ የሰብዓዊነት መርሀ ግብር ነው።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትንሸ የለውም፤ ከቅን ልቦና በመነጨ ለመልካም ስራ ዘወትር መተባበር የሰብዓዊነት የበጎ ፈቃድ አርበኛነት ነው፡፡ – የከንቲባ ጽ/ቤት