በአንድ ወቅት የሚያስፈራ የነበረው ስፍራ ዛሬ እንዴት የአዲስ አበባ ድምቀት ሆነ?

You are currently viewing በአንድ ወቅት የሚያስፈራ የነበረው ስፍራ ዛሬ እንዴት የአዲስ አበባ ድምቀት ሆነ?

AMN-መጋቢት 18/2018 ዓ.ም

በአንድ ወቅት የቆሻሻ መጣያ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ እና የወንጀለኞች መደበቂያ የነበረው የቁርጥሚ ወንዝ ዳርቻ፤ ዛሬ ተፈጥሮን ከዘመናዊነት ጋር አዋህዶ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎችና እንግዶች አስደናቂ የመዝናኛ አማራጭ ሆኖ ብቅ ብሏል።

ያ የቆሸሸ እና የሚያስፈራ የነበረው ስፍራ ዛሬ ታሪክ ሆኗል። በምትኩ በ21,906 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ዘመናዊ ፕላዛ እና የለመለመ አረንጓዴ ስፍራ ተተክቶበታል። ይህ የ2.2 ኪሎ ሜትር የቁርጥሚ ወንዝ ዳርቻ ልማት፣ መዲናዋን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በማስታረቅ ረገድ ትልቅ አሻራ ያረፈበት ፕሮጀክት መሆኑን ኤ ኤም ኤን ባደረገው የመስክ ቀኝት ተመልክቷል።

ይህ ሰፊ ስፍራ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ 4 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ደረጃውን የጠበቀ የእግረኛ መንገድ የተገነባለት ሲሆን፥ ሰዎች በቀን ሆነ በሌሊት በሙሉ ነፃነትና ምቾት ወክ እንዲያደርጉ ታስቦ የተሰራ ነው።

የተለያዩ የስነ-ጥበብ ጋለሪዎች፣ የባህል አልባሳት መሸጫዎች እና የተለያዩ ሱቆችን የያዘ በመሆኑ እንግዶች እየተዝናኑ የሚገበያዩበት ስፍራ ሆኗል።

የህጻናት መጫወቻ ስፍራዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ አምስት አምፊ ቲያትሮች እና ዘመናዊ ሬስቶራንቶች ተካተዋል። 7 ሄክታር መሬት የሚሸፍን አረንጓዴ ተክሎችና ዛፎች መዲናዋን ከተፈጥሮ ጋር አዋህደዋታል።

ከፕሮጀክቱ አስደናቂ ክፍሎች አንዱ ከመሬት በታች የተገነባው ባለ ሦስት ወለል የመኪና ማቆሚያ ሲሆን ይህም በአንድ ጊዜ 500 መኪናዎችን የመያዝ አቅም አለው። ዘመናዊ የዲጂታል ካሜራዎች እና የእሳት አደጋ መከላከያ ቴክኖሎጂ ተገጥሞለታል። ለወደፊቱ ታሳቢ ተደርጎ ለኤሌክትሪክ መኪናዎች የሚሆኑ ቻርጀሮችን አካቷል።

ይህ ፕሮጀክት ለመዲናዋ ነዋሪዎች ተጨማሪ የመዝናኛ ስፍራ ከመሆኑም ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረ፣ የአዲስ አበባ የከተሜነት ማሳያ መስታወት ነው።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review