AMN- መጋቢት 19 /2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአዲስ አበባ እጅግ ፈጣን የሆነ የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ መሙያ ጣቢያ አገልግሎት አስጀምሯል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው እንደ ሀገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ለማሳደግና ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት አገልግሎቱ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል::
በተለያዩ ድርጅቶች ለተገነቡ የኤሌክትሪክ ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች ተቋሙ ያልተቋረጠ የኃይል አቅርቦት እያደረገ እንደሚገኝ የገለጹት ኢንጂነር ጌቱ፣ በአዲስ አበባ 32 እንዲሁም በሌሎች ከተሞች ደግሞ 8 በድምሩ 40 የቻርጅንግ ስቴሽኖችን ለመገንባት በአቅድ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል::
የትራስፖርት እና ሎጅስቲክ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በርኦ ሐሰን በሶስት እና አራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ መንገዶች ላይ ከዜሮ ተነስተው ወደ 140 ሺህ የሚደርሱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ስራ ላይ እንዲውሉ መደርጉን ተናግረዋል። በሀገር ውስጥ ተሽከርካሪዎችን የሚገጣጥሙ ወደ 17 የሚጠጉ ተቋማት መፈጠራቸዉንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

2 ሺህ 300 ፋስት ቻርጂንግ ስቴሽኖችን የመገንባት እቅድ ተይዟል ያሉት በርኦ ሐሰን በአዲስ አበባ ብቻ 1 ሺህ 176 ቻርጂንግ ስቴሽኖች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል፡፡
በዘጠኝ ከተሞች የኤሌክትሪክ ባሶች ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ መደርጉን የገለጹት አቶ በርኦ፣ በአዲስ አበባ ብቻ ከመንግስት እና ከግል አጋሮች ጋር በመሆን ከ100 በላይ የኤሌክትሪክ ባሶች ወደ ስራ ገብተዋል ብለዋል።
ዜጎችም ከነዳጅ ጥገኝነት በመውጣት የኤሌክትሪክ መኪናዎችን መጠቀም እንዲጀምሩ ጥሪ ቀርቧል
በቴዎድሮስ ይሳ