በፊንቴክ ኢንቨስትመንት ድርጅት መስራችና ባለቤቶች ላይ ክስ መመስረቱን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ

You are currently viewing በፊንቴክ ኢንቨስትመንት ድርጅት መስራችና ባለቤቶች ላይ ክስ መመስረቱን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ

AMN መጋቢት 19/2018

በዜጎች ላይ የ1 ነጥብ7 ቢሊዮን ብር ጉዳት ባደረሱት የፊንቴክ ኢንቨስትመንት ድርጅት መስራችና ባለቤቶች ላይ ምርመራ አጣርቶ ለዐቃቤ ሕግ በመላክ ክስ የተመሰረተባቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል።

ፊንቴክ ኢንቨስትመንት የግል ድርጅት መስራችና ባለቤቶች ዳንኤል ዮሃንስ ኢየሱስ እና ግርማይ ገብረሚካኤል ይህደጎ የተባሉት ተጠርጣሪዎች ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን በመጠቀም ከ1 ሺህ 200 በላይ ዜጎችን በማጭበርበር ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ጉዳት በማድረሳቸው ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ለኤኤምኤን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው ተጠርጣሪዎቹ ላይ በ19 ዓይነት የተለያዩ ወንጀሎች ምርመራ አጣርቶባቸው ለዐቃቤ ሕግ በመላክ ክስ ተመስርቶባቸዋል።።

መጀመሪያ ክሱ የቀረበው ለአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ቢሆንም ምርመራው ውስብስብና ከፍተኛ ልምድ የሚጠይቅ ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑና በተደራጀ መልኩ መጣራት ስላለበት ጉዳዩን ወደ ኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በማምጣት ምርመራው በስፋት ሲጣራ መቆየቱን ፖሊስ ገልጿል።

ተጠርጣሪ ዳንኤል ዮሃንስ ላይ ክስ ተመስርቶበት ማረሚያ ቤት ሆኖ ክሱን እንዲከታተል መደረጉንና ተጠርጣሪ ግርማይ ገብረሚካኤልን ደግሞ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ክትትል እያደረገ መሆኑን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ግርማይ ገብረሚካኤል የተባለው ግለሰብ ከዚህ ቀደም እ.ኤ.አ አቆጣጠር በ2010 የደቡብ አፍሪካ የዓለም የእግር ኳስ ሻምፒዮና ወቅት አስካሉካን በተባለ ድርጅት ስም ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄዳችሁ የዓለም ዋንጫ እንድትመለከቱ አደርጋለሁ በማለት ዜጎችን አጭበርብሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ አሰባስቦ ከሃገር በመውጣት ተደብቆ እንደነበረ ፖሊስ አስታውሷል።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖል ጋር በመተባበር ባደረገው ጠንካራ ክትትል ከተደበቀበት ሀገር ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በሕግ አግባብ ተጠያቂ እንዲሆን ማድረጉን የወንጀል ሪከርዱ እንደሚያመላክትም አስረድቷል።

ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ተጎጂዎችን 50% ቅድመ ክፍያ 950 ሺህ ብር በማስከፈል በ90 ቀናት ውስጥ የመኪና ባለቤት እንደሚያደርጓቸውና ቀሪ 950 ሺህ ብር ደግሞ ያለወለድ በ5 ዓመት ተከፍሎ የሚያልቅ የባንክ ብድር እንደሚያመቻቹ በመግለጽ ዜጎችን በማጭበርበር ክፍያውን እንዲፈጽሙ አድርገዋል ሲል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገልጿል።

ተጠርጣሪዎቹ ኅብረተሰቡን ለማሳመን 148 መኪኖች ከጅቡቲ በማስገባት 100 መኪኖች ለተወሰኑ ግለሰቦች እንዲከፋፈል በማድረግ እና ቀሪ 48 ዘመናዊ መኪኖችን መርጠው በድብቅ መሸጣቸውን እንዲሁም ወደ ሀገር ውስጥ ስለመግባታቸው ምንም አይነት መረጃና ማስረጃ ሳይኖር 350 መኪኖችን ከውጭ እንዳስገቡ በማስመሰል ኅብረተሰቡን ሲያጭበረብሩ እንደነበር ፖሊስ በምርመራው አረጋግጧል፡፡

በተጨማሪም በጅቡቲ ወደብ ምንም ዓይነት መኪና ሳይኖር 400 መኪኖች ጅቡቲ ወደብ ላይ እንደቆሙና ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት በሂደት ላይ እንዳሉ በማስመሰል ለተጎጂዎች ሐሰተኛ መረጃ መስጠታቸውንም ፖሊስ ማረጋገጥ ችሏል።

በመስቀል አደባባይ ከተለያዩ ቦታዎች መኪኖችን በትውስት በማሰባሰብ ሕዝብን በሚያሳስት መልኩ ድርጅቱ ከውጭ ሀገር ያስገባቸው መኪኖች እንደሆኑ በማስመሰልና የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ከሆነው BYD ከተባለ የቻይና ካምፓኒ ጋር ምንም ዓይነት ውል ሳይኖራቸው ውል እንዳላቸው አድርገው የማጭበርበር ወንጀል ሲፈጽሙ መቆየታቸውንም ፖሊስ ጠቁሟል።

ተጠርጣሪዎቹ በጅቡቲ ውስጥ አልፋቲዞ በሚል ስም ድርጅት በማቋቋም BYD ከተባለ የቻይና ካምፓኒ ጋር አብሮ ከሚሰራ ሌላ ድርጅት ጋር በመነጋገር 10% ቅድመ ክፍያ በመክፈል የመጀመሪያዎቹን 148 መኪኖች ወደ ሀገር ውስጥ አስገብተው እንደነበርና ተጨማሪ 188 መኪኖችን በተመሳሳይ 10% ቅድመ ክፍያ ለድርጅቱ በመክፈል መኪኖቹን ተረክበው ወደ ሀገር ውስጥ ሳያስገቡ ጅቡቲ ላይ እንዲሸጡ ማድረጋቸውንና በአጠቃላይ 336 መኪኖችን 10% ጅቡቲ ለሚገኘው የቻይና ድርጀት በመክፈል ወስደው ቀሪ 90% ክፍያ አለመፈፀማቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ባደረገው ምርመራ ደርሶበታል።

ከ1 ሺህ 200 በላይ ተጎጂዎችን በማጭበርበር መዝግበው 95 ሺህ ብር ቅድመ ክፍያ፤ 285 ሺህ ብር የመንግስት ታክስ እንዲሁም 130 ሺህ ብር ለኤክትሪክ መኪና ቻርጀር ለማሰራትና ለባለሙያ በሚል ከእያንዳንዳቸው 1 ሚሊየን 365 ሺህ ብር መቀበላቸውን ፖሊስ አረጋግጧል፡፡

የፊንቴክ ኢንቨስትመንት ድርጅትን ባልተገባና በተጋነነ መልኩ በማስተዋወቅ በህገወጥ መንገድ ከተሰበሰበው ገንዘብ ተጋሪ በመሆን የተጠረጠሩ ሰለሞን ቦጋለ፣ ሰራዊት ፍቅሬ፣ ዳንኤል ተገኝ፣ አብርሃም ግዛው፣ ይገረም ደጀኔ፣ መንሱር ጀማል እና ካሊድ ናስር የተባሉ ታዋቂ አርቲስቶችና የማስታወቂያ ባለሙያዎችንም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎ ፍርድቤት በማቅረብ የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸው ፍርድ ቤትም እስከ መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም መፍቀዱ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በማጭበርበርና በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ (Money laundering) እና የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ጨምሮ በ19 የወንጀል ጉዳዮች በተጠረጠሩ የፊንቴክ ኢንቬስትመንት ድርጅት መስራቾችና ባለቤቶች ላይ እንዲመሰረት አድርጓል።

እንዲሁም ያላቸውን ዕውቅናና ተቀባይነት በመጠቀም ሆነ ብለው የተጋነነ ማስታወቂያ በመንገር እና በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ የሀሰት መረጃዎችን ለህብረተሰቡ በማሰራጨት ዜጎችን እንዲጭበረበሩ በማድረግ በሕገወጥ መንገድ ከተገኘው ገንዘብ እያንዳንዳቸው አሁን ባለው የገበያ ዋጋ ስምንት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቢ.ዋይ.ዲ ሶንግ ፕላስ የመኪና ስጦታ በመቀበል፤ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ (Money laundering) እና በዜጎች ላይ ከ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ በተጠረጠሩ አርቲስቶችና የማስታወቂያ ባለሙያዎች ላይ የጀመረውን ምርመራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

ይህ ውስብስብ የወንጀል ጉዳይ በተሳካ ሁኔታ ተጣርቶ ክስ እንዲመሠረት ከፖሊስ ጋር በትብብር ለሠራው የፍትህ ሚኒስቴር እና በጉዳዩ ላይ መረጃ ሲሰጥ ለነበረው ኅብረተሰብ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ላቅ ያለ ምስጋና አቅርቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review