የአዲስ አበባ መልክበከተሜነት መነፅር

You are currently viewing የአዲስ አበባ መልክበከተሜነት መነፅር

“በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ ግዙፍ የልማት ስራዎች ከውበት ባለፈ የዜጎችን አካላዊ፣ አእምሯዊና ስነ-ልቦናዊ ጤና ለመገንባት ታቅደው የሚተገበሩ ናቸው”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስም፣ አዲስ ነው፤ ያላረጀ ውበት፤ የዐይን ማደሪያ፤ አበባም አበባ፣ የቁንጅና ልኬት የንብ መነኸሪያ፡፡ በነዚህ ሁለት ጥምር ቃላት የምትጠራው አዲስ አበባ ደግሞ በብዙ መለኪያዎች በየዘመናቱ አዲስም፣ አበባም፣ ሆና እንደ ንጋት ጀምበር ደምቃ ትታያለች፡፡

በርግጥም አዲስ አበባ በዘመኗ አዲስም፣ አበባም እንደነበረች ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ዘመን እየገፋ አሳቢ እየጠፋ፣ አበባዋ እየጠወለገ፣ አዲስነቷ እያረጀ፣ እየደበዘዘ እና በስልጣኔ ምጥቀት እየተሻገረ መጥቶ ወደ ጎስቋላነት ተቀይሮ እንደነበርም የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡

በታሪክ መዝገብ ላይ በሰፈረው ገናና ክብሯ ግን አዲስ አበባ ዕድሜ፣ ወዝ፣ ለዛና ጣዕም ያላት ከተማ ናት፡፡ የሀገሪቱም ሆነ የአህጉረ አፍሪካ የስልጣኔ፣ የነፃነት፣ የአንድነት፣ የጀግንነት በር፣ የተስፋም መስኮት ናት፡፡

የከተሞች ከፍታና ዝቅታ ደግሞ እንደ ሀገር ያለው በረከትና መርገም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከተሞች የሀገራት ልብ ምት፣ የስልጣኔ መግቢያ በር፣ የምጣኔ ሀብት ርካብ፣ ቀን ነፍስና ስጋን ማስደሰቻ፣ ማታ ደግሞ ጨለማውን መርቻ የድል መቅረዝ ናቸው፡፡

የከተማ ኑሮ መሻሻል ምርታማነትን፣ ባህልን እና የሰው ልጆችን ደስታ ከፍ በማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት የከተማ ልማት ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ግሌዘር እ.ኤ.አ በጥር 31 ቀን 2012 ‘የከተሞች እውነት ወይም ድል’ (Triumph of the City) በተሰኘ ግሩም ጥናታዊ መፅሐፋቸው ላይ ገልጸውታል፡፡

በርካታ የዓለማችን ክፍል ቀን እንደነገሩ ውሎ አመሻሹን ሲያሸልብ ከተሞች ግን በተራራ ላይ እንደተለኮሰ ችቦ ብርሃንን እየፈነጠቁ በምድርቱ ላይ ያረበበውን ጨለማ እንደ አደይ አበባ በፈካ ውበታቸው እንዴት እንደሚገፍፉት ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ባማረ አገላለፅ፣ “ከተሞች የዓለማችን ሕይወት መቀጠል ምልክት፣ የልብ ትርታችን ምት ናቸው” በማለት በመፅሐፋቸው ከሽነውታል፡፡

ኒው ዮርክ ብዙ ጊዜ “ቀን ንቁ ማታ ደግሞ የማትተኛት ከተማ” እየተባለች ትጠራለች፡፡ ከተማዋ ቀን በተፈጥሮ ብርሃን ከፀሐይ ጋር ደምቃ ትውልና መሸት ሲል ደግሞ ከላይ በጨረቃና ክዋክብት፣ ከታች በዘመናዊ መብራቶች ትዋባለች፤ ትደምቃለች፡፡

አዲስ አበባም በዚህ ድል ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሆስፒታሊቲ እና የቱሪዝም ማኔጀመንት ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና መምህር ደመቀ ክብሩ እንደሚሉት በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለው ኮሪደር ልማት ከተማዋን ከቱሪስት መሸጋገሪያነት ወደ መዳረሻነት የቀረ፣ እንደ ኒው ዮርክ፣ ፓሪስና ለንደንን የመሳሰሉ ከተሞችን ፈለግ የተከተለ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ለአብነት የኮሪደር ልማቱ የከተማዋ የመንገድ መሰረተ ልማት እና የአረንጓዴ ሽፋን እጅግ ከፍ እንዲል አስችሏል። በከተማዋ ነባርና አዳዲስ ቱሪዝም መዳረሻዎች ዘመኑን በሚመጥን መልኩ ተገንብተዋል፡፡ ይህም ከቱሪዝም ኢኮኖሚው ባሻገር ለከተማዋ ነዋሪዎች አጠቃላይ ጤና ያለው ፋይዳ የላቀ መሆኑን ሁሉም የሚገነዘበው ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በኮሪደር ልማትና መሰል ተግባራት ከተማን ማዘመን ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ እና የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ  አስመልክቶ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል ይንገስ አለሙ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፣ በየትኛውም ሁኔታ፣ ከፍታና ዝቅታም ውስጥ ቢሆኑ ከተሞች ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ ስኬታማነት ያላቸው ሚና ላቅ ያለ ነው፡፡ በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ ስማርት መሆን ከከተማዋ ሁለንተናዊ ከፍታ ባሻገር እንደ ሀገር ትልቅ ኢኮኖሚያዊ እምርታ የሚያመጣ ነው ብለዋል፡፡

ከተሞች በዚህ ዘመን ላይ የስልጣኔ፣ የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሚባሉ ነገሮች ሁሉ ማዕከል ናቸው፡፡ በመሆኑም ከተማን ከስልጣኔ፣ ከዕድገት፣ ከልማት እና መሰል ዘመናዊ ነገሮች ልንለይ አንችልም ሲሉ አክለዋል፡፡

እንደ ይንገስ (ዶ/ር) በኮሪደር ልማቱም ሆነ በሌሎች ተግባራት ከተማዋ ስማርት ስትሆን የበለጠ ከተፈጥሮ ትታረቃለች፤ ከየትኛውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ሳይንስና ቴክኖሎጂን  በሁሉም ዘርፍ በመጠቀም ከዘመኑ ትወዳጃለች፤ ይህ ሲሆን ደግሞ የአገልግሎት ተደራሽነት ይሰፋል። ቅልጥፍናውም ይጨምራል፡፡ ዜጎችም ህይወት በብዙ መልኩ ይሻሻላል፡፡

ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት የከተማ ልማት ባለሙያና አማካሪ ኢንጂኒየር በሱፈቃድ ጌታቸው እንደሚሉት፣ የኮሪደር ልማቱ ካዛንቺስን፣ ዶሮ ማነቂያን፣ እሪ በከንቱን፣ ተረት ሰፈርን የመሳሰሉ የመዲናዋ አካባቢዎችን ውብ በማድረግ አዲስ አበባ የዘመናዊ ከተማ ገፅታን እንዲትላበስ አድርጓታል፡፡

እነዚህ  ሀሴትን የሚያጎናፅፉ የልማት ስራዎች ከተማዋን ከዓለማችን ፅዱ፣ ውብና ተመራጭ ከተሞች ተርታ የሚያሰልፉ ናቸው፡፡ በተለይም ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ደስተኛ ሕይወትን እንዲመሩ የሚያስችሉ ስለመሆናቸውም ጠቁመዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ ሁሉን ያቀናጀ የከተማ ግንባታ (smart city) አካል በመሆኑ ለዘመናዊ ከተማ ግንባታ እንደ ሀገርም ሞዴል ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የሰውና የተሽከርካሪ መጓጓዣ መንገዶችን፣ የፍሳሽ ማስወገጃ፣ የመብራት፣ የስልክ እና ኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታዎች፣ የመዝናኛና የማረፊያ ቦታዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እና መሰል የማህበረሰቡን ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችሉ መሆናቸው ደግሞ ስራውን የሚደነቅ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ 

ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሄር ‘ትኩሳት’ ብሎ በሰየመው መጽሐፉ ጀርባ ፒያሳ ሂድ፤ ፒያሳ ወደ ሕይወት ትመልስሃለች እንዳለው፡፡ ደራሲ መሐመድ ሰልማን ደግሞ ‘ፒያሳ ማህሙድ ጋ ጠብቂኝ’ በተሰኘ ድንቅ ድርሰቱ የፒያሳን ውበት እንደ ጅረት እያፈሰሰ፣ እንደ ወንዝ እያገማሸረ አስኮምኩሞናል፡፡

“ፒያሳ አንድ ሺህ አንድ መቶ ካፌዎች ያሉባት ቅመም የሆነች ሰፈር ናት” እንዲል፡፡ በእርግጥ ይህ በዘመኑ እውነት ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ዶሮ ማነቂያ የመሳሰሉ አካባቢዎች  እንደ ዘመኑ መዘመናቸው ቀርቶ ዘምመው አዲስ አበባም የትናንት ውበቷ በእርጅና ጉም ተሸፍኖ መልክና  ስሟ አልገጥም ማለቱ ብዙዎቹን ማስቆጨቱ የአዘቦት ተረክ ሆኖ መቅረቱም የማይካድ ሀቅ ነበር፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የአዲስ አበባ ፀሐይ ደመናውን ገፍፋ የታሪካችን እምብርት በሆነው በዓድዋ ድል መታሰቢያ በኩል አድርጋ ዳግም በፒያሳ ላይ ወጥታለች፡፡ በዚህ ስፍራ የወጣችው ጸሐይም ከአብርሆት ቤተ መፅሐፍት እስከ እንጦጦ ፓርክ፣ ከወዳጅነት አደባባይ በየ አካባቢው እስከተገነቡት ውብ፣ ፀአዳና ሰፋፊ መንገዶች እንዲሁም እንደ አዲስ በተወለዱት ቀበናን ወደ መሳሰሉ ወንዞች ድረስ የልማት ብርሃኗን እየፈነጠቀች ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉ ግዙፍ የልማት ስራዎች ከከተማ ውበት ባለፈ የዜጎችን አካላዊ፣ አእምሯዊና ስነ-ልቦናዊ ጤና ለመገንባት ታቅደው የሚተገበሩ መሆናቸውን ሰሞኑን ከቃና ቴሌቪዥን ጋር በከተማ፣ በከተሜነት፣ በክትመትና በኮሪደር ልማት ዙሪያ በነበራቸው ቆይታ የሰጡት ማብራሪያ አንዱ ምስክር ነው፡፡

ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን ማዕከል ያደረገው ይህ የልማት እንቅስቃሴ፣ ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲኖሯት በማድረግ ጤናማ የሆነ ማህበረሰብ ለመፍጠር ያለመ መሆኑንም ገልጸዋል።

ጤና ማለት የአካል ብቃት ብቻ ሳይሆን የአመጋገብና የዕለት ተዕለት የአኗኗር ዘይቤ ድምር ውጤት በመሆኑ፣ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችም ይህንን እሴት ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን አብራርተዋል። የአእምሮ ጤናንና የንባብ ባህልን ለማጎልበት የተገነቡት የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍትና የሳይንስ ሙዚየም ለነገዋ ኢትዮጵያ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑንም መስክረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ወጣቶች በምሽት ቤተ-መጻሕፍት ገብተው ሲያነቡ ማየት ትልቅ ብሔራዊ ተስፋ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሳይንስ ሙዚየም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ግምት የሚሰጠውና በሳይንስ የበለፀጉ ሀገራት መሪዎች ሳይቀሩ አድናቆታቸውን የገለጹበት ስራ መሆኑን አንስተዋል።

በሌላ በኩል፣ ኢትዮጵያ ያላትን ታላቅ ታሪክ የሚመጥንና ብሔራዊ ኩራትን የሚያጎለብቱ እንደ ዓድዋ ድል መታሰቢያና የቤተ-መንግስት ሙዚየሞች ያላቸውን ስልታዊ ጠቀሜታ አብራርተዋል።

ለአብነትም ከዚህ ቀደም ለውጭ ሀገር የክብር እንግዶች አበባ የሚቀመጥበትና የሀገርን ታሪክ የሚናገር ስፍራ አለመኖሩ ለኢትዮጵያ አሳፋሪ እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁን የተገነቡት የዓድዋ ሙዚየሞች ገንቢ ሀገራዊ ትርክት በማስረፅ ዜጎች በማንነታቸው እንዲኮሩና የአርበኝነት ስሜታቸው እንዲጎለብት እንደሚያደርግም ጠቅሰዋል፡፡

አዲስ አበባ እንደ ኒው ዮርክ፣ ፓሪስ እና ሪዮ ዲጄኔሮ ከተሞች የራሷ የሆኑ ዓለም አቀፍ መለያዎች (Landmarks) ሊኖሯት እንደሚገባ የተናገሩት ጠቅላ ሚኒስትሩ በተለይ በእንጦጦ እና በየካ አካባቢ የተሰሩ ስራዎች ከተማዋን እንደ ‘ሆሊውድ’ ያሉ ዓለም አቀፍ የቱሪስት መስህቦች ባለቤት እንደሚያደርጓት አመላክተዋል።

እነዚህ የልማት ስራዎች የቱሪስት መስህብ ከመሆን ባለፈ፣ አዲሱ ትውልድ የሀገሩን ማንነት አውቆ በኢትዮጵያዊነቱ እንዲኮራና የአርበኝነት ስሜቱ እንዲገነባ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። ይህ ከተማን ዘመናዊ የማድረግ ስራ የኢትዮጵያን የክብር ታሪክ ለዓለም በሚመጥን መልኩ ለማሳየት ያለመ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

አዲስም አበባም፤ የሆነችው አዲስ አበባ፣  ዘመኑን በዋጁ እና ጎስቋላነታቸውን በነበር እተኩ ባሉ ወንዞቿ፣ በሙዚየሞቿ፣ በመናፈሳቿ፣ በውብ ጎዳናዎቿ… የውበትን ሸማ ተጎናፅፋ አላፊ አግዳሚውን ከራሱ፣ ከተፈጥሮ እና ከዘመን ጋር እያስታረቀች መሆኑንም በርካቶች በመመስከር ላይ ናቸው፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review