AMN- መጋቢት 20/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎቿን ተከትሎ የዓለም አቀፍ ባለሀብቶችን ቀልብ መሳቧን ቀጥላለች።
ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተካሄደው ግዙፍ የኢንቨስትመንት ኮንፈረንስ፣ ሀገሪቱ በድምሩ 13 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ የኢንቨስትመንት ስምምነቶችን መፈራረሟን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን ጠቅሶ ቲ አር ቲ አፍሪካ ዘግቧል።
ይህ ግዙፍ የገንዘብ መጠን በተለያዩ ስትራቴጂካዊ ዘርፎች ላይ የሚሰማራ ሲሆን፣ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ፋብሪካዎች፣ የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጡና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች እና ለኢንዱስትሪ ሽግግር መሠረት የሆኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ዘገባው ጠቅሷል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ፣ ለእነዚህ ግዙፍ የኢንቨስትመንት ስምምነቶች ፊርማቸውን ካኖሩት መካከል የቻይና ኩባንያዎች የአንበሳውን ድርሻ ይዘዋል።
ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጠንካራ የንግድ ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክር እንደሆነም ነው የተገለጸው።
ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2024 ጀምሮ ተግባራዊ እያደረገችው ያለው ሰፊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ በተለይም የምንዛሬ ተመንን ነፃ ማድረግና የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረጓ ለዚህ ድል ዋነኛው ምክንያት መሆኑ ተመላክቷል።
ይህ 13 ቢሊየን ዶላር፣ ጎረቤት ሀገር ኬንያ ካስመዘገበችው 2.9 ቢሊየን ዶላር ጋር ሲነጻጸር፣ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን የኢንቨስትመንት ተመራጭነት በግልጽ የሚያሳይ እንደሆነም ዘገባው አያይዞ ጠቅሷል።
በታምራት ቢሻው