AMN – መጋቢት 20/2018 ዓ.ም
ለወራት በከባድ የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ የቆየውና የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበት የነበረው አንጋፋው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስተባባሪነት በተደረገለት የገንዘብ ድጋፍ ወደ ቀደመ ክብሩ እንዲመለስ የሚያስችለው አዲስ ተስፋ ተሰንቆለታል።
የክለቡ የቀድሞ ተጫዋቾች፣ አመራሮች እና ደጋፊዎች “ዛሬ ክለባችን ዳግም የተወለደበት ቀን ነው” ሲሉ ደስታቸውን ለኤ ኤም ኤን ገልጸዋል።
ክለቡ የገጠመውን ዘርፈ ብዙ ችግር ለመፍታት የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ቀዳሚውን ሚና መጫወታቸውን የክለቡ ማህበረሰቦች ተናግረዋል።
የክለቡን መፍረስ ለመታደግ ከንቲባዋ ለረጅም ጊዜ ደጋፊ ለነበሩት ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እና ቢጂአይ ኢትዮጵያ ያቀርቡትን ጥሪ ተቀብለው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ እንደገለጹት፣ ክለቡ ከፍተኛ የፋይናንሻል ድጋፍ ካልተደረገለት ከመፍረስ እንደማይድን ግንዛቤ በመወሰዱ፣ ከንቲባዋ ባቀረቡልን ጥሪ መሰረት ሚድሮክ ጊዜያዊ ችግሩን ለመፍታት ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።
በቀጣይም ደጋፊዎች ወደ አንድ መጥተው ትክክለኛ አደረጃጀት ከፈጠሩ ድጋፉ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የቢጂአይ ኢትዮጵያ ተወካይ አቶ አብዱልቃድር ማማ በበኩላቸው፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለእኛ ቤተሰባችን ነው፤ የከተማ መስተዳድሩ ጥሪ ሲያቀርብልን ቶሎ ለማገዝ ወስነን መጥተናል ሲሉ የኩባንያቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
የክለቡ ቡድን መሪ አዳነ ግርማ፣ ክለቡ ውስጥ የነበረው ችግር እጅግ አሳሳቢ እንደነበር አስታውሷል።
ለተጫዋች አራት እና አምስት ወር ደሞዝ አለመክፈል በጣም ከባድ ነው ያለው አዳነ፣ አሁን የተደረገው ድጋፍ ክለቡ ቀና ብሎ ወደ ቀደመ የአሸናፊነት መንፈሱ እንዲመለስ ትልቅ በር የሚከፍት መሆኑን ገልጿል።
የክለቡ ደጋፊዎች የተደረገውን ድጋፍ በታላቅ ደስታ ተቀብለውታል።
የክለቡ ደጋፊ ምንያህል ጌታቸው ዛሬ እኔ የተወለድኩበት ቀን ነው ማለት እችላለሁ ፤ ከንቲባዋ ‘ጊዮርጊስ ሀገር ነው’ ብለው ጊዜያቸውን መስዋዕት በማድረጋቸው ክለቡ ዳግም ተወልዷል ሲል ደስታውን ገልጿል።
ሌላው የክለቡ ደጋፊ መቶ አለቃ ነዋይ በበኩላቸዉ ቅዱስ ጊዮርጊስ የከተማዋ ክለብ ነው ፤ ከተማ አስተዳደሩ ስፖንሰሮችን በማስተባበር ላደረገው ነገር ከልብ እናመሰግናለን ብለዋል።
ሌሎች የክለቡ ደጋፊዎችም ይህ ቀን እንዲመጣ ብዙ ዋጋ ተከፍሏል ፤ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደሚገባው ክብር ይደርሳል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ይህ ድጋፍ የክለቡን የፋይናንስ ጫና ከመቅረፍ ባለፈ፣ በደጋፊዎችና በተጫዋቾች ዘንድ አዲስ ተነሳሽነትን የፈጠረ መሆኑ ተመላክቷል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ