የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጉዞ፦ ከዕይታ እስከ ድል!

You are currently viewing የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጉዞ፦ ከዕይታ እስከ ድል!

AMN- መጋቢት 22/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተጀመረው “ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ” (Homegrown Economic Reform) ተጨባጭ ውጤቶችን እያሳየ ይገኛል። መንግስት የኢኮኖሚው መሪነቱን ቀስ በቀስ ከመንግስት ወደ ግሉ ዘርፍ እንዲሸጋገር ትልቅ ትኩረት ሰጥቷል።

በዚህም ኢኮኖሚውን በቴክኖሎጂ በማዘመን ዲጂታል ኢትዮጵያን መፍጠር፤ የውጭ ኢንቨስትመንትን የሚስብ ክፍት የገበያ ስርአት መዘርጋት፤ ብድርን ለግሉ ባለሀብት በማመቻቸት የስራ እድልን ማስፋት የዘርፉ አበይት ዕይታዎች ናቸው።

በዚህም ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታት በኢኮኖሚው ዘርፍ እንደ ሃገር ሰፊ ስኬቶች ተመዝግበውበታል። ለአብነትም፦ ኢትዮጵያ ለዓመታት ለስንዴ ግዢ የምታወጣውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በማስቀረት፣ አሁን ላይ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጀምራለች። ይሄ በምግብ ዋስትና ረገድ ታሪካዊ ስኬት ነው።

አዲስ አበባን ጨምሮ በክልሎች የተገነቡት ፓርኮች (እንጦጦ፣ ወዳጅነት፣ አንድነት) እና የ”ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያን የአፍሪካ የቱሪዝም መዳረሻ እያደረጓት ይገኛሉ። ይህም ለሀገር ገጽታ ግንባታና ለገቢ ምንጭነት ትልቅ ሚና አለው።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የተራቆቱ መሬቶችን ማልማትና ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ተክሎችን ማስፋፋት ተችሏል።

በተጨማሪም በ​ሌማት ትሩፋት ስራዎች በዶሮ፣ በወተት፣ በማርና በሥጋ ምርት ላይ ትኩረት በማድረግ የቤተሰብን የተመጣጠነ ምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ስራ ተከናውኗል።

​ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታት ከፍተኛ ዕምርታ ካሳዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል ለዘመናት ተረስቶ የቆየው የማዕድን ልማት ዘርፍ አንዱ ነው። ከዚህ ዘርፍ፤ በወርቅ፣ በድንጋይ ከሰል እና በሌሎች ማዕድናት ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ በእጅጉ አሳድጓል።

በሌላ በኩል የታላቁ የህዳሴ ግድብ እውን መሆንን ተከትሎ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ለኢንዱስትሪ መስፋፋት ብቻ ሳይሆን፣ ለጎረቤት ሀገራት የኃይል ሽያጭ በማድረግ ለሃገር የውጭ ምንዛሬ ግኝትን አሳድጓል።

የፋይናንስ ዘርፍ ማሻሻያ እና ዲጂታላይዜሽን በተመለከተም የቴሌ ብር እና የባንኮች ቴክኖሎጂ መስፋፋት የገንዘብ ዝውውሩን ቀላልና ግልጽ ማድረጉ ለኢኮኖማው ዘርፍ ማበብ የተጫወተው ሚና ተኪ የሌለው ነው።

የማክሮ-ኢኮኖሚ ፖሊሲው ለውጥን ተከትሎ የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን መደረጉ በጥቁር ገበያ እና በህጋዊው ገበያ መካከል የነበረውን ልዩነት በማጥበብ፣ ለውጭ ኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

በሹመት ደመቀ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review