AMN- መጋቢት 24/2018 ዓ.ም
መጋቢት 24 ቀን 2010ዓ.ም. በኢትዮጵያየፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበትና አዲስ መንግስታዊ አመራር ስልጣን የተረከበበት ታሪካዊ ቀን ነው። ዕለቱ ኢትዮጵያ ወደ አዲስ ምዕራፍ የተሸጋገረችበትና ተስፋ የተሰነቀበትም ነው።
ከዚህ ዕለት ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት፣ የታሰሩ ፖለቲከኞችን ለመፍታት እና በውጭ ሀገር የሚገኙ የተቃዋሚ ሃይሎች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ በማድረግ ረገድ ሰፊ ስራዎች ተከናውነዋል።ይህም በሀገሪቱ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ አዲስ መንፈስ ከመፍጠሩም በላይ፣ የዜጎችን የመሳተፍ መብት ያረጋገጡ የሪፎርም እርምጃዎች የታዩበት መጀመሪያ ሆኗል።
በኢኮኖሚው ዘርፍ ኢትዮጵያየገጠማትን የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የዕዳ ጫና ለመቅረፍ “ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ” (HomegrownEconomic Reform) ተቀርጾወደ ስራ ተገብቷል። በዚህም መሰረት የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎች የተዘጋጁ ሲሆን፣ በተለይም በቴሌኮም እና በፋይናንስ ዘርፎች የታዩት ማሻሻያዎች ለውጭ ኢንቨስትመንት አዳዲስ በሮችን ከፍተዋል። ይህም ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን የኢኮኖሚ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ይበልጥ እንድታጠናክር ረድቷታል።

በዲፕሎማሲው መስክ ኢትዮጵያ ከአጎራባች ሀገራት ጋር የነበራትን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ አሳድጋለች። በተለይም ከኤርትራ ጋር ለሁለት አስርት ዓመታት የቆየውን የ “ሰላምም ጦርነትም የሌለበት” ሁኔታን በመስበር የተፈረመው የሰላም ስምምነት ለቀጠናው መረጋጋት ትልቅ ድል ነበር።
በተጨማሪም ሀገራችን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታና ድርድር ላይ የያዘችው ጽኑ አቋም እና የብሪክስ (BRICS) አባል መሆኗ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተሰሚነት እና የዲፕሎማሲ ልዕልና በግልጽ ያሳዩ ስኬቶች ናቸው። በአዲስ አበባ ባለፉት ዓመታት ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ለቱሪስቶች ሳቢ የማድረግ ስራዎች በከፍተኛ ፍጥነት ተከናውነዋል።
የእንጦጦ ፓርክ፣ የወዳጅነት ፓርክ እና የአንድነት ፓርክ ግንባታዎች ከተማዋን አረንጓዴ ከማልበሳቸውም በላይ፣ ለከተማ ነዋሪው የባህልና የመዝናኛ ስፍራዎችን ፈጥረዋል። እነዚህ ፕሮጀክቶች አዲስ አበባን በአፍሪካ ደረጃ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን ትልቅ አቅም ፈጥሮላታል።
የከተማዋን ገጽታ ሙሉ በሙሉ እየቀየረ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ ሌላኛው ጉልህ ስኬት ነው። ይህ ፕሮጀክት ያረጁና ለነዋሪዎች ምቹ ያልነበሩ መንደሮችን በማደስ፣ ሰፋፊ የእግር መንገድና የብስክሌት መስመሮችን በመዘርጋት እንዲሁም ዘመናዊ የመንገድ መብራቶችንና የፓርኪንግ ስፍራዎችን በማካተት ከተማዋን የዘመናዊነት ተምሳሌት አድርጓታል። ይህም የትራፊክ ፍሰቱን ከማቀላጠፍ ባለፈ የከተማዋን የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አነቃቅቷል።

በማህበራዊ ዘርፍ በአዲስ አበባ የተገነቡት ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች እጅግ የሚደነቁ ናቸው። በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የዳቦ ፋብሪካዎች፣ የተማሪዎች የምገባ ፕሮጀክቶች እና የአቅመ ደካማ ቤቶችን የማደስ ስራዎች መንግስት ለህዝቡ የሰጠውን ትኩረት ያሳየባቸው ናቸው። በተጨማሪም ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማት ግንባታ የከተማዋን ነዋሪ መሰረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት የተሄደበትን ርቀት ያረጋግጣሉ።
የከተማዋን የዕድገት ግስጋሴ የሚያፋጥኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እንደ የዓደዋ ድል መታሰቢያ፣ የሳይንስ ሙዚየም እና የአብርኾት ቤተ መጻሕፍት ፣ የሳይንስ ሙዚየም ግንባታዎች የኢትዮጵያን የታሪክ፣ የጥበብ እና የቴክኖሎጂ አቅም ለዓለም ያስተዋወቁ ስራዎች ናቸው። በተለይም የዓደዋ ድል መታሰቢያ የኢትዮጵያውያንን የድል ታሪክና የጥቁር ህዝቦችን ኩራት በዘመናዊ ጥበብ የዘከረ ሲሆን፣ ይህም ለአዲስ አበባ ታሪካዊና ስልጣኔያዊ ገጽታን ሰጥቷታል።
ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. ጀምሮየተመዘገቡት ስኬቶች ኢትዮጵያ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆናም ትላልቅ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደምትችል ያሳዩ ናቸው። በአዲስ አበባ የታዩት ለውጦችም የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ ማሳያዎች በመሆናቸው፣ እነዚህ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንዲውሉ የሁሉም ዜጋ የጋራ ድጋፍና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ በዛሬው ታላቅ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ጎልቶ ተሰምቷል።
በሹመት ደመቀ