AMN – መጋቢት 27/2018 ዓ.ም
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ ስፖርት ፓርክ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ የከተማዋን ነዋሪዎች የልማት ተጠቃሚነት ያረጋገጠ እና አካታች የሆነ ልማትን መሠረት ያደረገ ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ አካባቢውን ዳግም ሲያለማ ቀደም ሲል በስፍራው የነበሩ ነዋሪዎችን እና ነጋዴዎችን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።
ለአካባቢው ነዋሪዎች ዕጣ በማውጣት በስፍራው የተገነቡ ሱቆች ተላልፈውላቸዋል።
እነዚህ ሱቆች እንደ ሴራሚክ፣ መብራት እና ሌሎች የግንባታ ፊኒሺንግ ዕቃዎችን የሚሸጡ ነጋዴዎችን ዳግም ወደ ስራ ያስገቡ ናቸው።
የአካባቢውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቅረፍ እና የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማሳለጥ አዲስ የአውቶቡስ ተርሚናል በፕሮጀክቱ ተካቶ ተገንብቷል።

በተጨማሪም ከቀበና እስከ ግንፍሌ ወንዝ ያለው ዳርቻ በልዩ ውበት እንዲለማ ተደርጓል።
ይህ የወንዝ ዳርቻ ልማት ለአካባቢው ልዩ ፀጋ እና ውበት አላብሶታል ብለዋል ከንቲባዋ።
ይህ ስፖርት ፓርክ በተለይ ለህፃናት እና ለወጣቶች የተዘጋጀ መሆኑ ልዩ ደስታ እንደሚፈጥር የገለጹት ከንቲባ አዳነች፣ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ ያላትን አሸናፊነት ለማስቀጠል መነሻ የሚሆን ትልቅ ራዕይ የታየበት ነው ብለዋል።
በመጨረሻም ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቅ “እንችላለን” በሚል መንፈስ ሌት ተቀን ለሰሩ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ