AMN-ሚያዚያ 21/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ህጻናት ቦርቀዉ የሚጫወቱባቸው ከ5ሺህ በላይ የልጆች መጫወቻ ፣ እንክብካቤ የሚያገኙበት ከ1 ሺህ በላይ ዴይኬር ተገንብተዋል።
የአዲስ አበባ ህጻናት ት/ቤት ከመግባታቸው በፊት ተገቢውን የህይወት ጅማሬ እንዲኖራቸው፣ ከፅንስ ጀምሮ እስከ 6 ዓመት እድገታቸው የተስተካከለ እንዲሆን በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ተጠቃሚ ሆነዋል።

ወላጆችና አሳዳጊዎች ልጆቻቸውን የሚያውሉበት ቦታ እንዳይቸገሩ ፥ ልጆቻቸው እንክብካቤ የሚያገኙበት ዴይ ኬሮች ተገንብተው በርካታ ወላጆችና ህጻናት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
የከንቲባ አዳነች አቤቤ አበርክቶ የሆነው የ”ቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም” የከተማዋን ነዋሪዎች ማህበራዊ ደህንነት ለማረጋገጥ ከታለሙ ትላልቅ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ሲሆን ፤ ይህ የትውልድ ቀረፃ ህጻናት ሀገራቸውን መጥቀም በሚችሉት ሁኔታ ውስጥ እንዲያድጉ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ይገኛል።

የህጻናቱ የምግብ ድጋፍ እና በብዙዎች የከተማዋ ሰፈሮች ውስጥ ለህፃናት ደህንነቱ የተጠበቀ የመጫወቻና የመዝናኛ ስፍራዎችን መገንባትም ከዛሬ የህጻናቱ ቦርቀው ፤በምቹ ሁኔታ ውስጥ ማደግ ጀርባ ነገን ታሳቢ ያደረገው የአዲስ አበባ ትጋት ማሳያ ነው።
ቤት ለቤት በመሄድ ለህፃናት እና ለወላጆች የቅርብ ምክርና ድጋፍ የሚሰጡ 5 ሺህ ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጥቷቸው በሁሉም የከተማዋ ክፍሎች መሰማራታቸውን የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል።