“የመግባባት ዴሞክራሲ” ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ስብራት መፍትሔ!!

You are currently viewing “የመግባባት ዴሞክራሲ” ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ስብራት መፍትሔ!!

የመደመር መንግስት በኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ዘመናት የቆየውን የዴሞክራሲ ጥያቄና የትውልዶችን መሻት ከግብ ለማድረስ፣ “የመግባባት ዴሞክራሲ” ሞዴልን እንደ ዋነኛው የፖለቲካ ፈውስ ይመለከተዋል ። ፓርቲው ዴሞክራሲን ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ብልጽግና አንዱና ዋነኛው ምሰሶ አድርጎ የሚመለከተው ሲሆን፣ ይህንንም እንደ ስጦታ ሳይሆን እንደ ዜጎች መሠረታዊ መብት እንደሚቀበለው ገልጿል።

ቀደምት ሥርዓቶች ለዴሞክራሲ ግንባታ አስፈላጊ የሆኑ መደላደሎችን ሳይፈጥሩ መቆየታቸውና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማጣት ሂደቱን ወደ ኋላ ጎትቶት እንደነበር ፓርቲው በሰጠው መግለጫ አመልክቷል።

ከለውጡ በፊት የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ በበርካታ ተግዳሮቶች ውስጥ ያለፈ ሲሆን ፣ በተለይም የፌዴራሊዝም መርህ ከዴሞክራሲያዊ እሴቶች ጋር ተቀናጅቶ አለመሄዱ ትልቅ ክፍተት ነበር ። ለሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ የሚመጥን የዴሞክራሲ ሞዴል አለመፈጠሩ ሥርዓቱን ደካማ እንዲሆን አድርጎት ነበር ። በተጨማሪም የመብት ክርክሮች በብሔርና በባህል ማዕቀፎች ብቻ ተገድበው መቆየታቸው፣ መብቶችን እንደ መሠረታዊ የዜግነትና የሕግ ጥያቄ ለመመልከት እንቅፋት ሆኖ ነበር።

የለውጡ መንግስት ከውጭ የተኮረጁና የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘቡ ርዕዮተ-ዓለሞች ያስከተሉትን ውድቀት በማጤን፣ “የመግባባት ዴሞክራሲን” ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ተቃርኖ መፍትሔ አድርጎ አቅርቧል። ይህ ሞዴል ነባር ሥርዓትን ነቅሎ በአዲስ የመተካት ሳይሆን፣ በሂደትና በማሻሻያ የሚገነባ የረጅም ጊዜ ጉዞ ውጤት ይሆናል ። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዝኃ ማንነት ባላቸው ሀገራት፣ በፉክክርና በመገፋፋት የሚፈጠርን የፖለቲካ ውጥረት ወደ አማካኝና የተረጋጋ ሥርዓት ለማምጣት ያለመ ነው። የመደመር መንግስት አቋም በፉክክርና በትብብር መካከል ያለውን ሚዛን በመጠበቅ፣ የግለሰብና የቡድን መብቶችን በእኩልነት የሚያስከብርና በተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ ሥርዓት መገንባት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን ለማጠናከር በተወሰደው እርምጃ ተፎካካሪዎችን እንደ “አጋር” በመቁጠር፣ ከ64 በላይ ፓርቲዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ምህዳር ተፈጥሯል ። ከ275 በላይ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላትን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በማካተት የሥራ ኃላፊነት እንዲረከቡ መደረጉ ለዚህ ተግባራዊ ማሳያ ነው ። ከዚህም ባሻገር እንደ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ የሚዲያና የፍትሕ ተቋማትን ነፃና ገለልተኛ በማድረግ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት እየተጣለ ነው።

የሀገራችን ችግሮች የሚፈቱት ከውጭ በሚመጡ መርሆዎች ሳይሆን በሀገር በቀል ዕውቀትና በኢትዮጵያ ታሪክና ሥነ-ልቦና ላይ በተመሠረተ ሀሳብ ላይ እንደሆነ መገንዘብ ይገባል ። ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክር አሰባሳቢ ትርክት በመገንባትና የርዕዮተ-ዓለም አክራሪነትን በማስወገድ፣ በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ ዘርፎች ሁለገብ ልማትን ለማምጣት እየተሠራ መሆኑን ነው ። የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ስብራት በመጠገን፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነበትና ሁሉን አቀፍ የሆነ ዴሞክራሲን የዕለት ተዕለት የሕይወት እሴት በማድረግ በቁርጠኝነት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review