AMN- ሰኔ 10/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ኑሮ ለመደገፍ እንዲሁም ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል የ90 ቀናት ልዩ እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ተግባር መግባቱን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል።

ከንቲባዋ በየደረጃው ከሚገኙ አመራሮች ጋር በነበራቸው ስብሰባ ላይ እንደገለጹት፣ ይህ እቅድ የዜጎችን ተስፋ ከፍ የሚያደርግና በተለይም ለወጣቶችና ለሴቶች ልዩ ትኩረት የሰጠ መሆኑን አብራርተዋል።

በከተማዋ ለሚገኙ ወጣቶች የስራ እና የክህሎት ማሳደጊያ እድሎችን ማመቻቸት እንደሚገባ የገለጹት ከንቲባዋ፣ ወጣቱን በስፖርት፣ በባህልና ቱሪዝም ፕሮግራሞች እንዲሁም በየአካባቢው በተገነቡ አምፊቲያትሮች ሁልጊዜም ንቁ ተሳታፊ ማድረግ የሚያስችል እቅድ ሊኖር እንደሚገባም አሳስበዋል።

በመጪው የክረምት ወቅት 175 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር የታቀደ ሲሆን፣ ይህም በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎትና በሰፋፊ የግንባታ ስራዎች ላይ የሚመሰረት መሆኑ ተገልጿል።

በተለይም ከኮሪደር ልማትና በከተማዋ መሀል ከሚሰሩ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች ጋር ተያይዞ የሚመጡ እድሎችን ወጣቶች በስፋት እንዲጠቀሙባቸው በትብብር መስራት እንደሚገባ ከንቲባዋ አሳስበዋል።

ዝንባሌያቸውን በደንብ መለየትና ማሳተፍ ብሎም ክፍለ ከተሞችም ከተሰጣቸው መነሻ እቅድ ባለፈ በአካባቢያቸው ያሉትን ሰፋፊ እድሎች ማየት እንደሚጠበቅባቸውም ጨምረው ገልጸዋል።
በእቅዱ ላይ የተካተተው የሴቶች ተጠቃሚነት አሁንም ተጨማሪ አዳዲስ ፈጠራዎችንና ስራዎችን እንደሚሻ የጠቆሙት ከንቲባዋ፣ ከተለመዱት ዘርፎች ባለፈ ክፍለ ከተሞች አዳዲስ እድሎችን ማፈላለግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የመስሪያ ቦታዎችን አቅርቦት በተመለከተም፣ የተለመደውን አሰራር በመቀየር አዳዲስ ሼዶችና የስራ ቦታዎች መገንባት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
እንደ ማሳያም በቅጠል ተራ እንዲሁም ከቦሌ መድኃኔዓለም እስከ እንግሊዝ ኤምባሲ ባለው የጎላጎል መስመር በርካታ የስራ እድል የሚፈጥሩ ቦታዎች ተለይተው እንደሚሰሩና ቅድሚያም ለተነሺዎች እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።
በሚካኤል ህሩይ