AMN – ሰኔ 10/2018 ዓ.ም

የቤት እንስሳትን ማሳደግና መንከባከብ ለልቦናችን ደስታን ቢሰጥም፣ አስፈላጊው ጥንቃቄ ካልተደረገ ግን ህይወትን ለከፋ አደጋ የሚያጋልጡ በሽታዎች ተሽካሚ ሊሆኑ ይችላሉ።

በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ዋለልኝ አታላይ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ከእንስሳት ወደ ሰው ስለሚተላለፉ አደገኛ በሽታዎችና ስለመከላከያ መንገዶቹ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሐኪሙ እንደሚሉት፤ በቫይረስ፣ በፈንገስ እና በፓራሳይት አማካኝነት ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በርካታ በሽታዎች ያሉ ሲሆን፣ በተለይም ከሕፃናት ጋር ያለውን ከልክ ያለፈ ቀረቤታ መገደብና እንስሳቱን ማስከተብ ወሳኝ መሆኑን ያሳስባሉ።

የሰው ልጅና እንስሳት ባላቸው የዕለት ተዕለት መስተጋብር ምክንያት በሽታዎች በተለያዩ መንገዶች ሊተላለፉ ይችላሉ።
ለምሳሌ የምንመገባቸው የእንስሳት ተዋጽኦዎች (በተለይ ስጋ) በአግባቡ ካልተዘጋጁ፣ በቤት ውስጥ ለማዳ ብለን የምናሳድጋቸው እንስሳት በሚነክሱን፣ በሚቧጭሩን ወይም የሰውነት ፈሳሻቸው ከእኛ ጋር ንክኪ ሲፈጥር እና የእብድ ውሻ በሽታን እንደ ማሳያ የጠቀሱት ዶክተሩ በቫይረስ የሚመጣና እጅግ አስከፊ የጤና ቀውስ የሚያስከትል በሽታ ነው ብለዋል።

በተለይ የጎዳና ተዳዳሪዎች ከውሾች ጋር አብረው ስለሚኖሩ፣ ምግብ ስለሚሰጧቸውና ክትባት ስለማይወስዱ ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጡ ናቸው። ውሾች አንዴ በቫይረሱ ከተጠቁ ማንኛውንም ያገኙትን ሰው ሊነክሱ ይችላሉ።
በተለይ ውሻ በሚነክሰን ጊዜ ውሻው መከተቡን ካላወቅን፣ በሽታ ይኑርበትም አይኑርበትም እኛ ወዲያውኑ መድኃኒቱን መውሰድ አለብን። ካልሆነ ግን ያልጠበቅነው የሞት አደጋ ይከተላል ብለዋል።

ሌላው ያልተለመደውና ትኩረት የሚሻው የድመቶች ንክሻ ነው ያሉት ዶክተር ዋለልኝ፣ብዙ ጊዜ ትኩረት የማይሰጠው ነገር ቢኖር በድመቶች ንክሻ ወይም ጭረት የሚመጣው በሽታ ነው።
በተለይ የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎች በድመቶች አማካኝነት ለሚተላለፉ በሽታዎች ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው ብለዋል።
እንሰሳት ጋር ከልክ ያለፈ ቀረቤታ መስመር ሊኖረው ይገባል የሚሉት ሐኪሙ በተለይ ሕፃናት ከድመቶችና ከውሾች ጋር ያላቸው ቀረቤታ በጣም የላቀ ነው። ይሁን እንጂ ከቤት እንስሳት ጋር የሚኖረን ግንኙነት ጤናማና መስመር ያለው ሊሆን ይገባል። ካልሆነ ግን በሽታን በቀላሉ የማስተላለፍ ዕድሉ ሰፊ ነው።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ