የዛሬው አርበኝነት የዕድገት ተዋናይና የመዘመን መሪ መሆን ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ

You are currently viewing የዛሬው አርበኝነት የዕድገት ተዋናይና የመዘመን መሪ መሆን ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ

AMN ሚያዚያ 27/2018

85ኛው የድል በዓል በአዲስ አበባ አራት ኪሎ በሚገኘው የድል ሐውልት አደባባይ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ዕለቱ ፋሺዝምና ናዚዝም ድል የተመቱበት ታላቅ ቀን መሆኑን ገልጸው፣ ለመላው የሀገሪቱ ሕዝቦችና ለአርበኞች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያ ይህንን የድል በዓል የምታከብረው በአርበኞቿ ጽናትና በመራራ ተጋድሎ ነው ብለዋል።

አርበኞች በባዶ እግራቸውና ዝናራቸውን ታጥቀው ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታጠቀን ወራሪ ኃይል ማሸነፋቸው፣ የአንድነትን ኃይል ለዓለም ያሳየና የኢትዮጵያን ልዕልና በዓለም መድረክ ያስጠበቀ መሆኑን አብራርተዋል።

ይህም ድል የፋሺስት አስተሳሰብ ዳግም እንዳያንሰራራ መሠረት የጣለ መሆኑን ገልጸዋል።

ከአባትና እናት አርበኞች የተረከብነው ታላቅ ቅርስ ሰላም፣ ነፃነትና በራስ መተማመን መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ አርበኝነት የተረጋጋና የሰከነ የዕድሜ ዘመን ጸጋ ነው ብለዋል።

ይህ ታሪካዊ ድል ለሀገራችን ብልፅግናና ለወደፊት ተስፋችን ጽኑ መሠረት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

እያንዳንዱ ዜጋ በማስተዋልና አርቆ በማሰብ ሀገሩን ማገልገል እንዳለበት አስገንዝበው፤ የሕዝባችን ፍላጎት ማደግ፣ መሰልጠን እና መዘመን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

እንዲሁም የዛሬው አርበኝነት የዕድገት ተዋናይና የመዘመን መሪ መሆን እንደሆነ ገልጸው፤ ለሀገር የተከፈለውን መስዋዕትነት በማስታወስ ለተሻለች ኢትዮጵያ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review