ANM- ሚያዝያ 29/2018 ዓ.ም
ታሪካችንን በራሳችን አንደበት የምንነግርበትና የምንሰንድበት ጊዜ አሁን ነው ሲሉ የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ጉባኤ ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ፐልስ ኦፍ አፍሪካ (Pulse of Africa-POA) ከኤ.ጂ.ኤ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ (AGA-Tech) ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ይካሄዳል።
ጉባኤው አፍሪካውያን የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን በአንድ መድረክ በማግናኘት በአህጉራቸው የጋራ ትልሞች ላይ እንዲመክሩ የሚያስችል መድረክ ነው፡፡
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች ከአራቱም የአህጉሪቷ ማዕዘናት በመምጣት በውቧ አዲስ አበባ ከትመው የተለያዩ ሥራዎችን መጎብኘት ጀምረዋል፡፡

ከደቡብ ሱዳን የመጣችው የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪ አዲት ሱዛን ሰዎች ብዙ ጊዜ የአፍሪካን መጥፎ ገፅታ እንጂ ያላትን አቅም፣ ጸጋና በረከት አይነገርም ብላለች፡፡
አፍሪካ ከዓለም ማዕዘናት ሁሉም ሊጎበኟት የሚገባ ውብ አህጉር መሆኗን በመጥቀስ፤ ጉባኤው የአህጉሪቱ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን ወደ አንድ ማምጣቱ ያጋራ ትስስርን እንደሚያጠናክር ገልጻለች፡፡
ፐልስ ኦፍ አፍሪካ ከኤ.ጂ.ኤ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ጉባኤ የማህበራዊ ሚድያ ተጽእኖ ፈጣሪዎችን አንድ ማድረግ ያስችላል ብላለች።

ማላዊያዊው ኬቨን ጉምቢ (KBG) አፍሪካ ሁሉም ሀብቶች፣ የሚያምሩ ታሪኮች እና የውብ ጥበቦች አድባር የሆነች አህጉር መሆኗን ገልጿል፡፡
ብዙውን ታሪካችንን ሌሎች ሲነግሩን ቆይተዋል ያለው የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪው፤ ታሪካችንን በራሳችን አንደበት የምንነግርበትና የምንሰንድበት ጊዜ አሁን ነው ብሏል፡፡
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ይዞት የመጣው ሀሳብ ግሩም መሆኑን የገለጸው ደግሞ ከዩጋንዳ የመጣው የማህበራዊ ሚድያ ተጽእኖ ፈጣሪ ሞሰስ ኬዩኔ ነው።
አፍሪካውያን በዚህ መንገድ መገናኘታቸው እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ፣ ባህላቸውን እንዲጋሩ እና እንዲያሳድጉ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጿል።
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ እርስ በእርስ ለመማማር እና ልምድ ለመለዋወጥ ትልቅ እድል ይዞ መምጣቱን ተሳታፊዎች መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።