AMN- ሚያዝያ 29/2018 ዓ.ም
የመጀመሪያው የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ባደረጉት ጉብኝት፣ ተቋሙ እያከናወናቸው ባሉ ስራዎች መደነቃቸውን ገለጹ።
ጎብኝዎቹ በአውሮፓና አሜሪካ ብቻ ይገኛል ብለው የገመቱት አይነት የላቀ የቴክኖሎጂ ተቋም በአፍሪካ ምድር በማየታቸው ታላቅ ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
የኢንስቲትዩቱ የዋና ዳይሬክተር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እና የቴክኖሎጂ አማካሪ ሻምበል ይልማ(ዶ/ር)፤ ተቋሙ በጤና፣ ግብርና፣ ፋይናንስ፣ ሮቦቲክስ እና ስማርት ሲቲ ግንባታ ዘርፎች እያከናወናቸው ያሉትን ችግር ፈቺ ተግባራት ለተጽዕኖ ፈጣሪዎቹ አብራርተዋል።

በተለይም በአፍሪካ የመጀመሪያው የሆነው የኤ.አይ ዩኒቨርሲቲ መመስረት፣ አህጉሪቱ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲኖራት በማድረግ ረገድ ያለውን ቁልፍ ሚና አስገንዝበዋል።
ተሳታፊዎቹ በበኩላቸው፣ የኢንስቲትዩቱ ስኬቶች ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አርአያና የኩራት ምንጭ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ዩኒቨርሲቲው ስራ ሲጀምር የአህጉሪቱን የቴክኖሎጂ ተወዳዳሪነት ይበልጥ እንደሚያሳድገው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ይህ ጉብኝት ኢትዮጵያ በአፍሪካ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መሪ ለመሆን የምታደርገውን ጥረት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይበልጥ ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል የፈጠረ መሆኑን
ከኢንስቲትዩቱ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።