በመዲናዋ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ የተለያዩ ስትራቴጂዎች እየተተገበሩ ይገኛሉ – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- ሚያዝያ 30/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤዉን አድዋ ድል መታሰቢያ በሚገኘዉ የምክር ቤቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የከተማዉ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከመኖሪያ ቤት አቅርቦት ጋር ተያይዞ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩ የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ አምስት ስትራቴጂዎችን ቀርፆ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ቤቶቹም በመንግስት በጀት፤ በመንግስትና በግል ትብብር፤ በግለሰቦች፤ በሪል ስቴት (በድርጅቶች) ፤ ግለሰብ ከግለሰብ (መሬትና በጀት ያለዉ) በመቀናጀት የሚገነቡ መሆናቸዉን አንስተዋል፡፡

ባለፉት አምስት አመታት ከ480 ሺህ በላይ ቤቶች ተገንብተዉ ለነዋሪዎች መተላለፋቸዉን የተናገሩት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከነዚህ መካከል ከ139ሺህ በላይ የሚሆኑት ቤቶች ለቆጣቢዎች የተላለፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መሆናቸዉን አንስተዋል፡፡

አሁን ካለዉ ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት አንጻር በመንግስት በጀት ብቻ ፍላጎቱን ማሟላት አይቻልም ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ቀደም ሲል ተጀምረው የነበሩ ቤቶችን ከማጠናቀቅ ረገድ ግን ዉጤታ ስራዎች መከናወናቸዉን አንስተዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ያላቸዉን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍም በበጎ ፈቃድና በተለያዩ መርሃ ግብሮች በርካታ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review