በልጅነታቸው ከአርበኞች ጋር በዱር በገደሉ ዋጋ በመክፈል ለነጻነታቸው ተጋድሎ ሲያደርጉ የነበሩት አባት አርበኛ መኮንን መሸሻ…

You are currently viewing በልጅነታቸው ከአርበኞች ጋር በዱር በገደሉ ዋጋ በመክፈል ለነጻነታቸው ተጋድሎ ሲያደርጉ የነበሩት አባት አርበኛ መኮንን መሸሻ…

AMN – ግንቦት 02/2018 ዓ.ም

አባት አርበኛ መኮንን መሸሻ ከአባታቸው እንዲሁም ከአባት አርበኞች ልጅ ጓደኞቻቸው ጋር ሆነው በዱር በገደሉ እና በሌሊት ጨለማው ዋጋ በመክፈል ለኢትዮጵያ ነጻነት መከበር ድንቅ ተጋድሎ ሲያደርጉ እንደነበር ይናገራሉ፡፡

ኢትዮጵያ በጀግንነቷና በታሪኳ የምትታወቅ ሃገር ስትሆን ለዚህ ደግሞ ብዙ አባቶችና እናቶች የማይተካ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አባት አርበኛ መኮንን መሸሻ ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ለአምስት ዓመታት በነበረው ትግልና ፋሺስት ጣሊያንን ድል አድርገን እስከምናስወጣት ድረስ ከአባቴ ጋር ታግያለሁ ይላሉ፡፡

ከአባታቸው በወረሱት ጀግንነት በተለይም 1928 ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ትልቅ የአርበኝነት ተጋድሎ አድርገዋል፡፡ ከ100 ዓመት በላይ የእድሜ ባለጸጋ የሆኑት አባት አርበኛ መኮንን መሸሻ አዲስ አበባ ለገሃር የተወለዱ ሲሆን ጀግንነትን ከቤተሰቦቻቸው እንደወረሱ ይናገራሉ፡፡

በዚህም አባት አርበኛ መኮንን ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ልጅ እንደነበሩ በማስታወስ አያትና እናታቸው ለዘማች አርበኞች ስንቅ ያዘጋጁ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡

በወቅቱ ኢትዮጵያውያን የተደራጀ ዘመናዊ ትጥቅ አልነበራቸው የሚሉት አባት አርበኛ መኮንን ነገር ግን ያለውን ስንቅ፣ ጦር፣ እና ጎራዴ በመጠቀም በአንድነት ወደ ታወጀው ክተት አዋጅ አምርተዋል ብለዋል፡፡

በተለይም በ1929 ዓ.ም እነ አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ያቀጣጠሉትን የነፃነት ችቦ ተከትሎ ግራዚያኒ በኢትዮጵያውያን ላይ ግፍ መፈጸሙንም ያስታውሳሉ፡፡ በጊዜው እናቴ የግራ ጡቷ አካባቢ ተመታ ነበር ያሉት አባት አርበኛ መኮንን መሸሻ፤ ሌሎች ቤተሰቦቻቸው እና አርበኞችም ቆስለው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ፈተና ያልበገራቸው አባት አርበኛ መኮንንም ከአባታቸው እንዲሁም ከአባት አርበኛ ልጅ ጓደኞቻቸው ጋር ሆነው በዱር በገደሉ ዋጋ በመክፈል ለነጻነት ተጋድሎ ሲያደርጉ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ከምንጭ ውሃ መቅዳትን ጨምሮ ስንቅ የማቀበልና ሌሎች ተግባራትንም አከናውነናል፤ ስንቅ እንኳን ሲያልቅብን ፍራፍሬ ተመግበን ለሃገራችን ነጻነት ስንታገል ነበር ብለዋል፡፡

በመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ የንብ ቀፎ እና የጣሊያን ምሽግ እንደነበር በመግለጽም የፋሺስት ጣሊያን ወታደሮች አባታቸውን ለመያዝ ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው መጥተው እንደነበር ይናገራሉ፡፡

በዚሁ ወቅት አባታቸው ጥይት ሳያባክን የጣሊያንን ወታደሮች የንብ መንጋ በመልቀቅ ሲያባርር እና ከምሽግ ሲያስለቅቅ እመለከት ነበርም ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከሏት በእድሜ ቀዳሚ አንጋፋና የታሪክ አዋቂ የሆኑት አርበኛ መኮንን በወቅቱም በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ኢትዮጵያውያን የጣሊያንን የማታለያ ስልቶች ወደጎን በመተው በጽናት ታግለው ፋሺስት ጣሊያንን ድል እንዳደረጉም ያስታውሳሉ፡፡

አሁን ላይ ጀግና አባት አርበኞችን ለማስታወስና ለትውልድ ለመንገር በተሰሩ ስራዎች ደስተኛ መሆናቸውንም አባት አርበኛው ያነሳሉ፡፡

በሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review