አዲስ አበባ በቀዳማይ ልጅነት ያከናወነቻቸውን ተግባራት ለዓለም የምታስተዋውቅበት መድረክ ነገ ይጀመራል

You are currently viewing አዲስ አበባ በቀዳማይ ልጅነት ያከናወነቻቸውን ተግባራት ለዓለም የምታስተዋውቅበት መድረክ ነገ ይጀመራል

AMN – ግንቦት 02/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ ነገ ግንቦት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ከ20 በላይ ሀገራት የሚታደሙበትን የአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ለመጀመሪያ ጊዜ ታካሂዳለች። ከተማዋ ባለፉት ስድስትና ሰባት ዓመታት በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ባከናወነቻቸው ተጨባጭ ውጤታማ ሥራዎች ሳቢያ የአህጉሪቱን ትኩረት መሳብ ችላለች።

የአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ከነገ ግንቦት 3 እስከ ግንቦት 5 ቀን 2018 ዓ.ም ለተከታታይ 3 ቀናት ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚካሄድ በአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ማዕከል የፕሮግራሞች እና የአጋርነት ዳይሬክተር የሆኑት ናትናኤል አስረስ (ዶ/ር) ጠቁመዋል።

ናትናኤል አስረስ (ዶ/ር) ኮንፈረንሱ ሦስት ቀናት የሚቆይ መሆኑን ከ ኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ የገለጹ ሲሆን፣ ዓላማውም ሀገራት ልምዳቸውን የሚያካፍሉበትና አዲስ አበባ ያከናወነቻቸውን ስራዎች የምታሳይበት ክፍት የመማማሪያ መድረክ እንዲሆን ታስቦ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የማዕከል ፕሮግራሞች እና የአጋርነት ዳይሬክተሩ እንዳስታወቁት፣ አዲስ አበባ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ ሰፊ የዳሰሳ ጥናት ካካሄደች በኋላ በስትራቴጂክ ፕሮግራም ማኔጅመንት ኦፊስ አማካኝነትና በከንቲባ አዳነች አቤቤ ቀጥተኛ መሪነት፣ ከተለያዩ የሴክተር ቢሮዎች ጋር በቅንጅት ሰፊ ሥራ ስታካሄድ መቆየቷን አንስተው ይህም እስካሁን ተጠናክሮ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህም የመጫወቻ ቦታዎችን ማስፋፋት፣ በጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች ውስጥ ቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራምን ማካተት፣ በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች የጨዋታ-ተኮር ካሪኩለም መዘርጋት፣ እንዲሁም የመምህራንና የርዕሰ-መምህራን አቅም ማጎልበት ዋነኛ ትኩረቶቹ እንደሆኑ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ኮንፈረንሱ ፕሮፌሰሮችን፣ ሚኒስትሮችን፣ የፓርላማ አባላትንና ከንቲባዎችን ጨምሮ ከአፍሪካ ከኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳ፣ ጋና፣ ሴኔጋልና ዛንዚባር፤ እንዲሁም ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ ብራዚል፣ ቺሊ እና ከሌሎችም ሀገራት የተወጣጡ ከፍተኛ አመራሮች እና ባለሞያዎች ልምዳቸውን እንደሚያካፍሉ ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ከሆነ፣ ኮንፈረንሱ አራት ዋና ዋና ምሰሶዎችን ማዕከል ያደረገ ሲሆን፣ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና አመራር፣ ዘላቂ የሀገር ውስጥ ፋይናንስ፣ በጥናት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ አሰጣጥ፣ እና የሰው ሃይል ልማት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ አመላክተዋል።

አዲስ አበባ ራሷን የምታቀርበው ብቸኛዋ ስኬታማ ሞዴል አድርጋ ሳይሆን፤ ‘እኛ ይህን ያህል ሠርተናል፣ ከእናንተም ተሞክሮ እንማራለን’ በሚል መርህ የመማማሪያ እና ልምድ የመለዋወጫ መድረክ እንደሚሆን ነው ዳይሬክተሩ ያስታወቁት።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review