የመደመር መንግሥት የኢኮኖሚ ሥርዓት ከምግብ ዋስትና የተሻገረ፣ የዜጎችን የምርጫ አድማስ የሚያሰፋ እና የበለጸገ ኢኮኖሚ የመገንባት ግብ ሰንቋል። ይህን ዓላማ ለማሳካት ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገትና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋገጥ፣ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ገበያ-መር የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት በቁርጠኝነት እየተሠራ ይገኛል።
ለዚህም ግንባታ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ለውጥን የሚያረጋግጥ የብዝኃ ዘርፍ የልማት ስትራቴጂ ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን፣ ይህም በተለይ የመንግሥትን ሚና የገበያ ጉድለትን ከመሙላት ባለፈ የግል ዘርፉ እንዲያብብ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠርና ቅርፅ ከማስያዝ አኳያ ይተረጉመዋል። የመደመር መንግሥት ገበያው ለውድድር ክፍት እንዲሆን ሲደረግ ፣ በተጓዳኝ ደግሞ ተጋላጭ ዜጎችን የመጠበቅና ሥርዓት የማስያዝ ሚናውን በብቃት እንደሚወጣ ይታመናል።
ካለፈው መዋቅራዊ ችግርና የዕዳ ጫና በመውጣት፣ ኢኮኖሚው በአቅርቦትና ፍላጎት፣ በገቢና ወጪ፣ እንዲሁም በቁጠባና ኢንቨስትመንት መካከል የነበሩበትን የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶች ለማስተካከል ሰፋፊ ሥራዎች ተከናውነዋል። የግል ዘርፉን እንደ ኢኮኖሚው ዋና ሞተር በመቁጠር፣ ለ60 ዓመታት ያገለገለው የንግድ ሕግ እንዲሻሻል ተደርጓል፤ እንዲሁም የስታርትአፕ አዋጅን ጨምሮ በርካታ የሕግ ማሻሻያዎች ተተግብረዋል። ለግልና ለውጭ ኢንቨስትመንት ዝግ የነበሩት እንደ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ የባንክ ዘርፍና የካፒታል ገበያ ለውድድር ክፍት መደረጋቸው መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ የነበረውን ውጤታማ ያልሆነ ጣልቃ ገብነት በመቀነስ ለግል ዘርፉ ሰፊ ዕድል ለመፍጠር ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።
የመንግሥት የኢኮኖሚ መፍትሔዎች በአንድ ርዕዮተ-ዓለም የታጠሩ ሳይሆኑ፣ በተግባር በሚታይ ውጤት ላይ የተመሠረቱና “ገቢር ነበብ” የተሰኘ የኢኮኖሚ ፍልስፍናን የሚከተሉ ናቸው። ይህም ከጽንፈኛ ወግ አጥባቂነት የወጣ፣ ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበና በፈጠራ የታጀበ አሠራርን ያሰፍናል።
የመደመር መንግሥትን የመገንባት ዕሳቤም እንደ አንድ ባለሀብት የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ የሚተጋ፣ መጪውን ጊዜ በሚገባ በመተንበይ የፈጠራ መፍትሔዎችን የሚያመጣና ሥርዓታዊ ፍጥነትን የሚያረጋግጥ ነው። ይህ ሥርዓታዊ ፍጥነት ሊረጋገጥ የሚችለው የመንግሥት ቢሮክራሲ፣ የግል ዘርፉና ሌሎች ተዋንያን እርስ በርሳቸው ተናበውና ተቀናጅተው መሥራት ሲችሉ ብቻ እንደሆነ ይታመናል።
ሀገራችን የባከነባትን ዘመናትና የተከማቸባትን ውዝፍ ሥራ ለማቃለል መንግሥት “መፍጠር፣ መፍጠንና መዝለል” የሚሉ ሦስት ቁልፍ ምሰሶዎችን እንደ ዋና የልማት ስልቶች ወስዷል። የፈጠራ መንገድ ምርታማነትን በማረጋገጥ ኢትዮጵያን ከጥሬ ዕቃ አቅራቢነት ወደ ምርት ባለቤትነት ለማሸጋገር ሲረዳ፣ የፍጥነት መንገድ ደግሞ የሥራ ቅደም-ተከተልን በመለየትና የጊዜ አጠቃቀምን በማጥበቅ የኋላውን ለማካካስ ያስችላል።
የዝላይ መንገድ የበለጸጉ ሀገራት ያለፉባቸውን አዝጋሚ የደረጃ በደረጃ ዕድገቶች በመዝለል ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በቀጥታ በመቀላቀል ፈጣን ለውጥ ማምጣትን ያለመ ነው። በእነዚህ ስልቶች አማካኝነት የማይበገርና በዓለም ተወዳዳሪ የሆነ ኢኮኖሚ በመገንባት የዜጎችን የኑሮ ውድነት ለማቃለልና ሁለንተናዊ ብልፅግናን በአንድ ትውልድ ዕድሜ ውስጥ እውን ለማድረግ በትጋት እየተሠራ ይገኛል።
See less