ከይዞታ ማረጋገጫ፤ ከግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር እንዲሁም ከመሬት ማስተላለፍ ጋር ተያይዘው የሚነሱ የአገልግሎት ማነቆዎችን በዘላቂነት ለመቅረፍ እየተሰራ ነዉ

AMN ሐምሌ 11/2018 ዓ.ም

ከይዞታ ማረጋገጫ፤ ከግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር እንዲሁም ከመሬት ማስተላለፍ ጋር ተያይዘዉ የሚነሱ የአገልግሎት ማነቆዎችን በዘላቂነት ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ መኮንን ያኢ ለኤ ኤም ኤን እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ የመሬት ወረራን ጨምሮ ሊከሰቱ የሚችሉ የመሬት ማጭበርበር ወንጀሎችን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል የቴክኖሎጂ አቅም ተገንብቷል፡፡

ቴክኖሎጂን መሰረት በማድረግ እየተሰሩ ባሉ የአገልግሎት ስራዎችም የሰው ንክኪ መቀነሱን፤ ከይዞታ ማረጋገጫ፤ ከግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር እንዲሁም ከመሬት ማስተላለፍ ጋር ተያይዘው ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎች መፍትሔ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡

የመሬት አገልግሎትን ይበልጥ ለማሳለጥ እየተሰሩ ካሉ ስራዎች ባሻገር ሌብነት እና ብልሹ አሰራርን በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስና ተጠያቂነትን ለማስፈን እየተሰራ መሆኑንም ነው ኃላፊው የተናገሩት፡፡

ቢሮው የሚሰጣቸውን ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት እየገቡ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ በሚቀጥሉት 90 ቀናት 14ቱንም አገልግሎቶች በሁሉም ማዕከላት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ከመሬት እና ይዞታ ነክ አገልግሎቶች ከአምስት ቢሊየን ብር ያልበለጠ ገቢ ሲገኝ እንደነበረ አውስተው፤ በ2018 በጀት ዓመት ገቢው ከ19 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ላይ መድረሱን አስረድተዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review