AMN ግንቦት 7/2018 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ባለፉት ዓመታት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምክክር ሂደቱ ወደፊት እንዲራመድ በትዕግስት እና ከፍ ባለ የሞያ ስነ-ምግባር በማከናወን አሁን ያለበት ምዕራፍ ያደረሱትን ሁሉንም ኮሚሽነሮች አመሰግናለሁ ብለዋል፡፡

የምክክር ባህል እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት እጅግ አስፈላጊ ነው። ጠንካራ የሲቪክ ማኅበረሰብ ባህል ግንባታ ደግሞ ያላሰለሰ የመነጋገር ልምምድ እና የሰከነ የወል መደማመጥን ግድ ይላል። የእስካሁን ሂደቱም በማኅበረሰባችን በየደረጃው የመደማመጥን ከፍ ያለ ጠቀሜታ አሳይቷል። ሂደቱ በሀገራችን ሁሉም ማዕዘናት የሚገኙ ከ90 በመቶ በላይ ኢትዮጵያዊያንን አመለካከቶች እና የውይይት ውጤቶች ያንፀባረቀ ሆኗል ብለዋል፡፡

ለሀገር ወሳኝ ፋይዳ የያዘው የምክክሩ ምዕራፍ ተጨባጭ ውጤት ወደሚያስገኘው ቀጣይ ምዕራፍ በሚሸጋገርበት በዚህ ወቅት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለሀገራችን ሰላም፣ አንድነት እና ዘላቂ መረጋጋትን የሚያረጋግጥ የጋራ ፅኑ አቋም እና ገንቢ በሆነ መንገድ አስተዋፅኦ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መልእክት አስተላልፈዋል፡፡