AMN- ግንቦት 9/2018 ዓ.ም
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልእክት እንደገለጹት በጠቅላይ ሚኒስትራችን ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የገጠር ኮሪደር ዋና ዓላማ የገጠር ማኅበረሰብን የኑሮ ዘይቤ መቀየር፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም አርሶ አደሩ የተሻለ ሕይወት እንዲመራ ማስቻል ነው ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም በሶፊ ወረዳ ቡርቃ ቀበሌ በፍጥነት፣ በጥራትና የአካባቢውን አፈርና ድንጋይ በመጠቀም በህብረተሰቡ እውቀት የተሠሩ ሥራዎች ለዚህ ትልቅ ማሳያ መሆናቸውን ተመልክተናል ብለዋል።
በሞዴል መንደሩ የተገነቡት ቤቶች የሰዎችን ማደሪያ ከሕፃናትና ከከብቶች ቤት የለዩ፣ የዶሮ እርባታ፣ ሻወርና ሽንት ቤት እንዲሁም የጓሮ የሌማት ትሩፋትን ያካተቱ ሙሉ ፓኬጅ አላቸው።

የገጠር ኮሪደር ልማት የአርሶ አደሩን ጉልበትና ሀገር በቀል ዕውቀት በመጠቀም፣ በአነስተኛ ወጪ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።